ቅዳሜ ጥቅምት 10 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በምእራብ ሽዋ ዞን በአቡና ግንደ በረት ወረዳ ፋጅና ጌርጌራ በተባሉ አካባቢዎች ላይ ጥቃት የሰነዘረው የሸኔ ቡድን በክፍለ ጦሩ የሠራዊት አባላት መደምሰሱን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አስታውቋል።
በሽብር ቡድኑ ላይ በተወሰደው ርምጃ የቡድኑ ከፍተኛ አመራር የሆነው ጃል ቦሩ አምቦ እንዲሁም ሌሎች በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የተለያዩ የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎችን እና ተኳሾችን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉም ተነግሯል፡፡
በተመሳሳይ በጀልዱ ወረዳ በጩልቄ እና በሽኩቴ አካባቢዎች ላይ የሽብር ቡድኑ በሰነዘረው የማጥቃት ሙከራ እቅዱ ሳይሳካ ቀርቶ ሰራዊቱ የቡድኑን እኩይ ተግባር ቀድሞ ማክሸፍ መቻሉን ሻምበል ከረሚላ ሙሃመድ ገልፀዋል።
ሰራዊቱ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጠናዎች አንፃራዊ ሰላም በማምጣት በጸጥታ ችግር ምክንያት አገልግሎት አቋርጠው የነበሩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ወደ ቀደመ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ፤ ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝም መከላከያ ሰራዊት አስታውቋል።



