ረቡዕ ጥቅምት 14 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) አንጋፋው ተመራማሪ ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ የአሜሪካን ብሄራዊ የሳይንስ ሜዳሊያ ሽልማት ከፕሬዚደንት ጆ ባይደን እጅ ተቀብለዋል።
በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ዘርፍ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉ የአሜሪካ ዜጎች በሚሰጠው በዚህ ሽልማት 19 ሰዎች የተካተቱ ሲሆን፤ የፐርዱ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባው ፕሮፌሰር ጋቢሳ ከተሸላሚዎቹ አንዱ ሆነዋል።
መምህርና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ጋቢሳ ኤጄታ ለሽልማቱ ያበቃቸው በከፍተኛ የምርምር ሥራቸው የእፅዋት ዘረመል ምህንድስና በመጠቀም በረሃማ የአየር ንብረት እና ነፍሳትን የሚቋቋሙ የአዝርዕት ዘሮችን በማግኘታቸው ሲሆን፤ ግኝታቸው በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ ዋስትና እንደሚያረጋግጥ ታምኖበታል።
ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጄታ በዕጽዋት ዘረመል ማዳቀል እና ዓለም አቀፍ ግብርና ተመራማሪ፣ የፑርዱ ግሎባል የምግብ ዋስትና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ፤ የፑርዱ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ዋስትና ፕሬዚደንት ባልደረባ ናቸው።
ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጄታ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለአየር ንብረት ተስማሚ የግብርና ቴክኖሎጂና የብዝሀ ሕይወት ጥበቃ የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል እንዲቋቋም አስተዋፅዖ አድርገዋል።
በማሽላ እህል ላይ ሰፊ ጥናት ያደረጉት የዓለም ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጄታ፤ እ.አ.አ በ2009 የከፋ ድርቅ እና አጥፊ አረምን የሚቋቋሙ የማሽላ ዝርያን ላይ ባደረጉት ምርምር የዓለም ምግብ ሽልማትን ተቀዳጅተዋል። ይህ ምርምራቸው ከፍተኛ የማሽላ ምርትን በመጨመር ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመመገብ ረድቷል።
በተጨማሪም የአገራችንን አርሶ አደሮች ሕይወት ለመቀየር ላበረከቱን አስተዋፅዖ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸው እንደነበር ይታወሳል።



