“ኢትዮጵያ በኃይልና በወረራ ማሳካት የምትፈልገው አንዳች ነገር የለም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ በኃይልና በወረራ ማሳካት የምትፈልገው አንዳች ነገር የለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያስፈልገናል የሚል ሃሳብ ስታነሳ ወረራ ሊካሄድ ነው የሚል ስጋት የሚያነሱ መኖራቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ኢትዮጵያ በኃይልና ወረራ ማሳካት የምትሻው አንዳችም ነገር የለም” ብለዋል።

አክለውም፤ የመከላከያ ሰራዊት ቀን ለጋራ ጥቅም፣ ዕድገትና ብልጽግና ኹሉንም አሸናፊ በሚያደርግ መርህ የጋራ ጥቅም የምናስከብር እንጂ፤ በኃይል ፍላጎቶቻችንን ለማሳካት ፈፅሞ አናስብም ሲሉም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ያሉት በዛሬው ዕለት ለ116 ጊዜ “በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚጸና የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ሀሳብ በመስቀል አደባባይ በተለያዩ ዝግጅቶች በተከበረበት መድረክ ላይ ነው።በመድረኩም “ኢትዮጵያ ማንንም ወርራ አታውቅም የመውረር ፍላጎትም የላትም፡፡ ኢትዮጵያ በወረራ የምታሳከው ፍላጎትም ሆነ ልማት የለም”፤ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የመከላከያ ሰራዊት መቶ ዓመታትን በተሻገረ ታሪኩ አገሩን ከጥቃት መከላከል እንጂ ማጥቃት ዓላማ አድርጎ የማያውቅ መሆኑን አስታውሰዋል።

“መከላከያ የጠፋን ሰላም ለማምጣት የሚተጋ ፤ ያለን ሰላም ለማስጠበቅ የሚታትር፤ ለሉአላዊነት መሥዋዕትነት የሚከፍል የአገር ዘብ የኩራት ምንጭ ነው፡፡” ሲሉም ገልጸዋል።

“አገራችን በወራሪዎች ተሸንፋ አታውቅም አሁንም አትሸነፍም፤ በዉጊያ ተሸንፈንም፣ ተንበርክከንም አናውቅም፤ ታሪካችን የሚያሳየን ማሸነፍን፣ ማንበርከክን ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡

አገርን መጥላትና ተቋምን ማፍረስ በብዙ የአፍሪካ አገራት እንደታየው ኹሉ በኢትዮጵያም በርካታ ያልተሳኩ ሙከራዎች መኖራቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ኢትዮጵያንና ተቋሞቿን፣ የዜጎቿን አብሮነት ማፍረስ ያልተገባ ተግባር በመሆኑ ትምህርት ሊወሰድበት ይገባል፡፡” ብለዋል።

የተከበረ ተቋም የሆነው የአገር መከላከያ ሰራዊትንና ኢትዮጵያን ማጽናትና መጠበቅ እንደሚያስፈልግም ያስገነዘቡም ሲሆን፤ የትኛውንም አይነት ልዩነት በንግግር፣ በውይይትና በድርድር መፍታት መለመድ እንዳለበት አንስተው፤ “መገዳደል መቆም አለበት” ሲሉ አሳስበዋል።ጥቅምት 15 ቀን 1900 የጦር ሚኒስቴር የተቋቋመበትን ዕለት ታሳቢ በማድረግ በዛሬው ዕለት በተካሄደው የሠሪት ቀን መርሃ ግብር ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ፣ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የተለያዩ አገራት የጦር አዛዦች፣ የጦር መኮንኖችና ሌሎች እንግዶች ታድመዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here