በትግራይ ክልል በስምንት ወራት ከ200 ሺሕ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸው ተገለጸ

አርብ ጥቅምት 16 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በትግራይ ክልል ከጥር ወር 2015 እስከ መስከረም 2016 ድረስ 204 ሺሕ 398 ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን የአለም የጤና ድርጅት ገልጿል።

በክልሉ በአብዛኛው የሰሜን ምዕራብ እና ማዕከላዊ ዞኖች የወባ ወረርሽኝ የተስተዋለ ሲሆን፤ በተለይም በአስር ቀበሌዎች ውስጥ በስፋት መስተዋሉ ነው የተገለጸው።

እንደ ድርጅቱ ገለጻ ለወባ ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ቅድመ ምርመራ በማድረግ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ቢሆንም፤ አሁንም 1 ሚሊየን 95 ሺሕ የወባ በሽታ መመርመሪያ መሳሪያዎች በአካባቢዎቹ ያስፈልጋሉ፡፡

እንዲሁም ከሚያስፈልገው 3 ሚሊየን 21 የጸረ ነፍሳት አጎበር ውስጥ፤ 1 ነጥብ 268 ሺሕ አንድ መቶ አስራ ኹለት አጎበሮችን ለ35 ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ወረዳዎች ማድረስ መቻሉን አመላክቷል።

በከፍተኛ ኹኔታ ተጋላጭ የሆኑ አስር ወረዳዎች ላይ የ100 ሺሕ አባወራዎችን ቤት የኬሚካል ርጭት መካሄዱንም ገልጿል።

በተመሳሳይ፤ ክልሉ ከወባ ወረርሽኝ ቀጥሎ በኹለተኛ ደረጃ እየተጠቃ የሚገኘው በመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን በሽታ ሲሆን፤ በአጠቃላይ 152 ሺሕ 872 ያህል ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተገልጿል፡፡ እንዲሁም በበሽታው ምክንያት የ74 እናቶች ሞት መመዝገቡ ተመላክቷል።

ድርጅቱ በአጠቃላይ 911 ሺሕ ለሚሆኑ በተለያዩ በሽታዎች የተጠቁ የክልሉ ነዋሪዎች፤ የሕይወት አድን የሕክምና አገልግሎ በ28 የድርጅቱ አጋር ተቋማት በኩል መሰጠቱን አስታውቋል።

እንዲሁም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 956 ሜትሪክ ቶን የሕክምና እርዳታ በክልሉ ለሚገኙ የሕክምና ተቋማት ማድረሱን የገለጸው የአለም የጤና ድርጅት፤ በዚህም ኹለት ሚሊየን የሚጠጉ የክልሉ ነዋሪዎች የሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን አመላክቷል፡፡

በጦርነቱ ሳቢያ የወረርሽኝ መከላከል እርምጃዎች በመቋረጣቸው ምክንያት፤ በክልሉ የኮሌራ እና ኩፍኝ ወረርሽኞች የመስፋፋት እድል ከፍተኛ ነው ሲልም አሳስቧል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here