ሐሙስ ጥቅምት 22 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን እና እገታዎች፤ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልል መንግሥታት በቂ የሆነ ትኩረት አልሰጧቸውም ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አስታወቀ፡፡
ኢሰመጉ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ፤ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በአገሪቷ እንዲሁም በውጭ አገር ዜጎች ላይ በታጠቁ ቡድኖች እየተፈጸመ ያለው እገታ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ያስታወቀ ሲሆን፤ ይህም ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰትን እያስከተለ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
“መንግሥት ያለበትን የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ ባለመሆኑ፤ ዜጎች በሚታገቱበት ወቅት በአጋቾች በሕይወት የመኖር መብታቸው፣ የአካል ደህንነት፣ ማሰቃየት ወይም ሌላ ጭካኔ የተሞላበት እና ኢሰብአዊ አያያዝ ወይም ቅጣት እንዳይደርስባቸው የመጠበቅና እና ሌሎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንደሚጣሱ መረዳት ይቻላል” ሲልም ኢሰመጉ በመግለጫው ጠቁሟል።
ይህም ዜጎች ደህንነት እንዳይሰማቸው ያደረገ በመሆኑ በነጻነት ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር እና የዕለት ተግባራቸውን ለመከወን ተግዳሮት እየሆነባቸው በመልገጽ፤ በስጋት እንዲኖሩ ያደረጋቸው መሆኑንም አስገንዝቧል፡፡
እነዚህ የእገታ ድርጊቶች የሚፈጸምባቸው አካባቢዎች በተደጋጋሚ ጊዜ እገታ የሚፈጸምባቸው ቦታዎች መሆናቸው እየታወቅ ዘላቂ መፍትሔ ባለመሰጠቱ፤ በአካባቢዎቹ የሚኖሩ ሰዎች እንዲሁም የሚዘዋወሩ ሰዎች የእገታ ሰለባ መሆናቸውን የገለጸው ኢሰመጉ፤ ይህም ድርጊት ቁጥራቸው አነስተኛ የማይባሉ ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ምክንያት መሆኑን አመላክቷል፡፡
ኢሰመጉ በዚሁ ዙሪያ ዝርዝር መረጃዎ እንዳሉት የገለጸ ሲሆን፤ እነዚህን መረጃና ማስረጃዎች በማደራጀት ዘገባዎችን በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝም ጠቁሟል።
በፌደራልና በክልል የሚገኙ የሚመለከታቸው የመንግሥት የጸጥታ አካላት ለማህበረሰቡ በቂ ጥበቃ በማድረግ ከስጋት ነጻ የሚሆኑበትን መንገድ እንዲያመቻቹም ኢሰመጉ በመግለጫው ጥሪውን አቅርቧል፡፡



