ሐሙስ ጥቅምት 22 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ከአምስት ሚሊየን በላይ ሰዎች ከድርቅ ጋር ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች መጎዳታቸውን፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) አስታወቀ።
ማስተባበሪያ ቢሮው በኢትዮጵያ ያለውን አጠቃላይ የሰብዓዊ ኹኔታ አስመልክቶ፤ ከክላስተር አስተባባሪዎች እና ከሰብአዊ ድጋፍ አድራጊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የኹለት ሣምንት ሪፖርት በትናንትናው ዕለት ይፋ አድርጓል።
በሪፖርቱም በአየር ንብረት መቀያየር፣ በእርስ በእርስ ግጭቶች እንዲሁም በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት፤ በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ ኹኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ጠቁሟል፡፡
በመላ አገሪቱ የበልግ እና የክረምት ዝናባማ ወቅቶች የተሻሻለ የግብርና ምርት እና በቂ የዝናብ መጠን ማሳየቱን የገለጸው ማስተባበሪያው፤ ነገር ግን በዋና አጋሮች ይደረግ የነበረው የምግብ ድጋፍ መቋረጡ፣ ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መኖሩና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመላክቷል።
በዚህም ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ከ10 በመቶ በላይ የሚሆነው የምግብ እርዳታ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ እንደሚፈልግ የገለጸው ማስተባበሪያው፤ ሌሎች ከ4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕርዳታዎች እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቋል፡፡
ማስተባበሪያው በሪፖርቱ በአማራ ክልል በተለይም በሰሜን ጎንደር፣ በሰሜን እና ደቡብ ሸዋ እንዲሁም በኦሮምያ ልዩ ዞን ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ሊኖሩ የሚችሉ ተረጂዎችን ለመለየት እና ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የዳሰሳ ጥናት መደረጉን የገለጸ ሲሆን፤ ሆኖም በገጠር አካባቢዎች የሚደረገውን እንቅስቃሴ በማሳደግ አሁንም ተጨማሪ ክትትል እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።
በዚህም በክልሉ ከሦስት ነጥብ አምስት ሚሊየን በላይ ሰዎች በእርሻ ሰብል መጎዳት፣ በእርሻ ግብዓት እጥረት፣ በተባይ መሰራጨት እንዲሁም በክልሉ በመካሄድ ላይ ባለው የትጥቅ ግጭት ምክንያት ለተረጅነት መጋለጣቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
የፌደራሉ መንግሥት ይህንን ችግር ለመቅረፍ በሰሜን ወሎ 170 ሺሕ ለሚጠጉ እንዲሁም በደቡብ ወሎ ለሚገኙ 35 ሺሕ ተፈናቃዮች አስቸኳይ የምግብ ርዳታ ማድረጉን የገለጸው ማስተባበሪያው፤ ነገር ግን አሁንም በክልሉ 1 ሺሕ 700 ተፈናቃዮች አስቸኳይ የምግብ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁሟል፡፡ እነዚህን ዜጎች በዕርዳታው ለማካተት እየተሰራ መሆኑንም ገልጿል።
በተጨማሪም በትግራይ ክልል የተደረገው ዳሰሳ የመኸር እርሻ ምርት መጠን ከአማካኝ በታች እንደሚሆን በማሳየቱ፤ ከኹለት ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች የምግብ እጥረት ችግር እንደሚያጋጥማቸው ማስተባበሪያው አመላክቷል።
እንዲሁም በቀጣዮቹ ወራት በክልሉ 50 በመቶ የእንስሳት መኖ እጥረት ሊኖር እንደሚችልም ጠቁሟል፡፡
የፌደራል መንግሥቱ በክልሉ የተከሰተውን የምግብ እርዳታ እጥረት ለመሸፈን በተቻለው አቅም ጥረት እያደረገ መሆኑን የጠቆመው ቢሮው፤ በዚህም በ24 ወረዳዎች ለሚገኙ 361 ሺሕ ተጎጂ ተፈናቃዮች የምግብ እርዳታ ማቅረቡን አስታውቋል።
እንዲሁም በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ በ65 ወረዳዎች ለሚገኙ 750 ሺሕ ሰዎች ኹለተኛ ዙር የምግብ እርዳታ መጀመሩን በመግለጽ፤ ከነዚህም እስከ ጥቅምት አጋማሽ ድረስ በሦስት ወረዳዎች ለ800 ሰዎች እርዳታ መደረጉን አመላክቷል።
በተመሳሳይ በአፋር በኦሮሚያ በሱማሊ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ተመሳሳይ የድርቅ አደጋዎች መከሰታቸውን የገለጸው የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ፤ በአገሪቱ ኮሌራ፣ ወባ እና ኩፍኝ ዋና የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ሆነው መቀጠላቸውንም በሪፖርቱ አስታውቋል።



