በቀጣዮቹ አስር ቀናት አንዳንድ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተጠቆመ

0
157

ሐሙስ ጥቅምት 22 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በቀጣዮቹ አስር ቀናት አንዳንድ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ የሚኖራቸው ሲሆን፤ በጥቂት ስፍራዎቻቸው ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

በመደበኛ ኹኔታ በሕዳር የመጀመሪያዎቹ አሥር ቀናት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ኹኔታ እንደሚያመዝን የገለጸው ኢንስቲትዩቱ፤ በተጨማሪም በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚዘወተር አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በጋ ኹለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ለዝናብ መኖር አመቺ ኹኔታ የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በይበልጥ ተጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ የትንበያ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ኹኔታም በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ እና በምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎቹ አሳይተዋል፡፡

በተጨማሪም በጸሀይ ኃይል ታግዘው ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በተለይም በደቡብ ምዕራብና በጋ ኹለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የተስፋፋና ሰፊ ቦታዎችን የሚያካትት ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል በመካከለኛው፣ በምስራቅ እና በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ከሚጠናከሩት የአየር ኹኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ይኖራል፡፡

በአጠቃላይ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ኹሉም የወለጋ ዞኖች፣ ጅማ፣ ኢሉባቦር፣ ቡኖ በደሌ፣ ሁሉም የአርሲ፣ የባሌና የጉጂ ዞኖች፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ የቦረና ዞን፤ ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም፣ መካከለኛው፣ ሁሉም የጎንደር ዞኖች፣ የባህር ዳር ዙሪያ፣ አዊ ዞን መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ የቤንሻንጉል ክልል ዞኖች፣ የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የሱማሌ ክልል ዞኖች እንዲሁም ሐረሪ እና ድሬዳዋ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች ጥቂት ስፍራዎቻቸው ላይም ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ኢንስቲዩቱ አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም የጋምቤላ ክልል ዞኖች፤ የመካከለኛው ኢትዮጵያ ክልል፤ የሰሜን እና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ አዲስ አበባ፣ ኹሉም የሸዋ ዞኖች፣ የምዕራብ፣ የሰሜን ምዕራብና የደቡብ ትግራይ ዞኖች እንዲሁም ከአፋር ክልል ዞን 3፣ 5 እና 1 በአንዳንድ ሥፍራዎቻቸው ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚያገኙ ተመላክቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here