ሐሙስ ጥቅምት 22 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ እዝ በሰራው ሥራ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ከመፍረስ ታድጓል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡
ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ “እራሱን በፋኖ ስም የሚጠራው ፅንፈኛ ቡድን የአማራ ሕዝብ ጥያቄን ሽፋን በማድረግ በሕዝብ ይሁንታ የተመረጠን መንግሥት ኢ-መደበኛ ወይንም ኢ-ሕገመንግሥታዊ አካሄድን በመከተል በሃይልና በነፍጥ፣ በሁከትና በግርግር በመታገዝ በመጀመሪያ አማራ ክልልን ቀጥሎም የፌደራል ስርዓቱን በማፍረስ የራሱን እኩይ ኢኮኖሚያ እና ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ለማሳካት ያለመ እንደነበር በተደጋጋሚ ጊዜ መንግሥት ሲገልጽ ነበር” ሲሉ አስታውሰዋል፡፡
ቡድኑ የደቀነውን አደጋ ለመቀልበስም በወቅቱ መደበኛ በሆነ የሕግ ማስከበር አካሄድ መቆጣጠር እንደማይቻል በመረጋገጡ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት እና የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ጠቅላይ መምሪያ እዝ በማደራጀት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባቱንም ገልጸዋል፡፡
አዋጁንም ስኬታማ ለማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ እዙ እራሱን በልዩ ልዩ አደረጃጀቶች አደራጅቶ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መግባባት ተፈጥሮ ወደ ሥራ መገባቱንም ሚኒሰትሩ አስረድተዋል፡፡
በየጊዜውም በክልሉ እና በአጎራባች አካባቢዎች የተወሰዱ የኦፕሬሽኖችን እርምጃዎች፣ የተጣሉ ክልከላዎች፣ በቀጣይ የተደረጉ ማሻሻያዎች እንደዚሁም የተገኙ ውጤቶች ለሕዝቡ መረጃ ይፋ ሲደረግ መቆየቱንም የገለጹት ዶ/ር ለገሰ፤ ክልሉን ወደ ነበረበት ሰላማዊ ኹኔታ ለመመለስ የተደረጉ ጥረቶችን እና የአመራር መልሶ ማደራጀትንም በተመለከተ ለሕዝቡ ግልፅ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በትናንትናው ዕለትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ እዝ የእስካሁኑን አጠቃላይ የትግበራ እንቅስቃሴ በጥልቀት መመርመሩን በመግለጽ፤
“በዚህም ግምገማ ማረጋገጥ የተቻለው ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ከመፍረስ መታደጉን ነው” ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ “በክልሉ የተጠናከረ አመራር እንዲደራጅ እና የክልሉን ሕዝቦች መሰረታዊ ጥቄዎች ለመፍታት የሚያስችል ቁመና እንዲላበስ መደረጉን እዙ በግምገማው አረጋግጧል” ሲሉ በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡



