ሰኞ ጥቅምት 26 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በጦርነት ላይ ከምትገኘው ሱዳን ኢትዮጵያዊያንን የማስወጣት ስራ እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባጋራው ጽሑፍ፤ ጥቅምት 23/2016 ተመላሾችን ያሳፈሩ አራት አውቶቡሶች ከካርቱም ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መደረጉን አመላክቷል።
ይህን ሥራ ለመስራት ብሔራዊ ግብረ ኃይል የተቋቋመ ሲሆን፤ ተመላሾች ወደ የቤተሰቦቻቸው እስከሚደርሱ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።
ከአሁን በፊት ከ34 ሺሕ 700 በላይ ኢትዮጵያውያን ከጦርነት ቀጠና ወጥተው ወደ አገራቸው መግባታቸውንም ሚኒስቴሩ አስታውሷል፡፡
ስድስተኛ ወሩን ያስቆጠረው የሱዳን ጦርነት በየዕለቱ ለንጹሀን ዜጎች ሞት መንስኤ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን እስከአሁን ከ 5ሺህ በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ 12 ሺህ ያህል ሰዎች መቁሰላቸውን እንዲሁም 5 ነጥብ 7 ሚሊየን ያህሉ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ባወጣው ሪፖር ማስታወቁን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።



