ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በቅርቡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ራስ-ገዝ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ለትርፍ ካልተቋቋመው እና በትምህርት ዘርፍ ላይ ከተሰማራው ከቱርኩ ማዕሪፍ ፋውንዴሽን ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በታሪኩ ወደ አዲስ ምዕራፍ ሽግግር በሚያደርግበት ወቅት የስትራቴጂክ ትብብር እና አጋርነትን በማስፋትና በማጠናከር በአካዳሚ፣ በልማት እና በቢዝነስ ረገድ ያሉትን እንቅስቃሴዎች ከአጋሮቹ ጋር በአዲስ መንፈስ ማጠናከሩ፤ ራስ-ገዝ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲነቱን ይበልጥ እንደሚያጠናክርለት አስታውቋል
በዚህም ለትርፍ ካልተቋቋመቀው እና በትምህርት ዘርፍ ላይ ከተሰማራው ከቱርኩ ማዕሪፍ ፋውንዴሽን ጋር አዲስ የአጋርነት ፊሪማ መፈራረሙ አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጿል።
ስምምነቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርቲ ተጠባባቂ ፕሬዝደንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እና በቱርኩ ማዕሪፍ ፋውንዴሽን ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ዶ/ር ቢሮል አኩን አማካይነት የተፈረመ ሲሆን፤ ይህ አጋርነት የዩኒቨርሲቲውን የዓለም አቀፍ፣ ክልላዊ እና ብሔራዊ አጋርነቶችን በአዲስ መልክ ማስፋፋትና ማጠናከር እንደሚያስችል ተመላክቷል፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከድርጅቱ ጋር የዘረጋው አዲስ የትብብር መስክ የተባባሪዎችን፣ የለጋሾችን እና የደንበኞችን ቁጥር ከፍ በማድረግ ወደ ሙሉ ራስን-ገዝነት የሚያደርገውን ጉዞ ለማፋጠን እንደሚረዳው ጠቁሟል፡፡
የቱርኩ ማዕሪፍ ፋውንዴሽን በዓለም ዙሪያ ከ104 በላይ በሚሆኑ አገሮች ውስጥ የሚሰራ የትምህርት ተቋም ነው፡፡



