አርብ ታህሳስ 5 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የኅብረት ሥራ ማህበራት ለዘላቂ እድገት በሚል መርህ ለአምስተኛ ጊዜ በአዳማ ከተማ አባ ገዳ አዳራሽ ተከብሯል።
የኅብረት ሥራ ማህበራት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ውስጥ ያላቸውን ድርሻ በመረዳት፣ የኅብረት ሥራ ማህበራት በህብረት እንዲንቀሳቀሱ ማስቻልና የባለድርሻ አካላቱን ሚና ከፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኅብረት ሥራ ማህበራትና አርሶ አደሮች ያለባቸውን የፋይናንስ ተደራሽነት ችግር ለመቅረፍና የገጠሩን ኢኮኖሚ መደገፍን አልሞ የተመሰረተው የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በሥራ ዓለም ለ19 ዓመት በተጠጋ ቆይታው በኅብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅቶ መቆየቱ ተመላክቷል።
እንዲሁም ማህበራቱ በዩኒየኖች ለተዋቀሩት አርሶ አደር ከማስያዣ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት፤ የምርት ዕሴት ሰንሰለትና የገበያ ትስስር በመፍጠር ብሎም በምርታቸው ላይ ዕሴትን በመጨመር የሚገባቸውን ገቢ እንዲያገኙ፣ ንግዳቸውን እንዲያስፋፉና በዓለም አቀፍ ደረጃም መነገድ እንዲችሉ በገንዘብ በመደገፍና በሙያ ምክር በማገዝ ባደረጋቸው ጥረቶች ውጤት መምጣቱ ተገልጿል፡፡
የኅብረት ሥራ ማህበራት አርሶ አደሮችን አቅም ለማጠናከር ላለፉት አራት ዓመታት ለ1ሺህ193 ማህበራትና 12ሺህ አርሶ አደሮች ብር 32 ሚሊዮን ወጪ የቢዝነስ አሠራራቸውን ላማሻሻል የሚያስችል ስልጠና ለመስጠት መቻሉ ተጠቁሟል፡፡
የዓለም አቀፍ የኅብረት ሥራ ማህበራት ኅብረት መረጃ እንደሚያሳየው ዓለም በአቀፍ ደረጃ የኅብረት ሥራ ማህበራት ብዛታቸው ከ3 ሚሊዮን በላይ ሲሆን አባላቶቻቸው ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ እንደሚሆኑ ይገልጻል።


