ከወራት በፊት መቀሌ ከተማ የተቋቋመውን እና በዋናነትን የፌዴራል ስርአቱን ከአህዳዊ ስርአት ለመታደግ በሚል የተደረገው ጉባኤ ቀጣይ የሆነ የምክክር መድረክ በመጪው ሳምንት ማክሰኞ በመቀሌ ከተማ ስድስት መቶ ሰዎች በተገኙበት ሊካሔድ ነው፡፡
ከሃይማኖት አባቶች፣ ከምሁራን እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች አምስት አምስት ሰዎች ከመላው ኢትዮጵያ ተውጣጥተው የሚሳተፉበት ይህ ጉባኤ፣ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡበት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ ርእስ ዙሪያ ብዙ የሚጣረሱ ሐሳቦች ያሏቸው ሰዎች ስላሉ በተለይም ፌዴራሊዝም ይቀራል አይቀርም የሚለውን እንዲሁም የሚጎለብት ከሆነም እንዴት በሚለው ዙሪያ ለኹለት ቀናት በመቀሌ ከተማ እንደሚመክርም የአስተባባሪ ኮሚቴው አባል የሆኑት የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ ፕሬዝዳንት የሆኑት ልጅ መስፍን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ይህ ጉባኤ ላለፉት 28 ዓመታት በኢትዮጵያ ሲተገበር የቆየውን የፌዴራል ስርአቱን ወደ አሃዳዊ ስርዓት ያመጣል የሚል ሐሳብ ያላቸው ኀይሎች ስላሉ፣ በዚህ ላይ ሰፊ ምክክር ለማድረግ በሚል የሚዘጋጅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ጉባኤውን የሚመሩት በኮሚቴ የተደራጁ ምሁራን እና ፖለቲከኞች እንዲሁም በመቀሌ ከተማ የሚኖሩ ግለሰቦች መሆናቸውን የገለጹት ልጅ መስፍን፣ የፋይናንስ አማራጮችንም ያሰባሰቡት እኚሁ የኮሚቴ አባላት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ምርጫ ቦርድ በጠራው ስብሰባ ላይ የታየውን ከፍተኛ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ተጨማሪ ሰዎችን እንድንጋብዝ በቀረበልን ጥሪ መሰረት ተጨማሪ ተሳታፊዎችን ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋበዝን ሲሆን፣ ይህም የተሳታፊውን ቁጥር ከስድስት መቶም ሊያልቀው ይችላል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
‹‹ሕገ መንግሥት እና ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ስርዓት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ የሚዘጋጀው ይህ ጉባኤ፣ በርካታ ፓናሊስቶች እና ምሁራን በጉዳዩ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚያቅረቡበት እና በተለይም ራስን በራስ ማስተዳደር ላይም እንደሚመክር ተናግረዋል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012



