“መልክዓ ምድራዊ ፌዴራሊዝም” መፍትሔ ወይስ ቅዠት?

0
901

ብሔርን መሰረት አድርጎ የተዋቀረው የፌዴራል ሥርዓት በርካታ ክፍተቶች እንዳሉበት እሙን ነው የሚሉት ሚኒልክ አሰፋ፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በሚል በሕዝቦች ፍላጎት ላይ ያልተመሰረት የፌዴራሊዝም ሥርዓት ለመተግበር መሞከር ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። በአገራችን የፌዴራል ሥርዓትን መተግበር የሚያስፈልጋት ብዝኀነትን ለማስተናገድ መሆኑ እስከታመነ ድረስ የፌዴራል አወቃቀሩን ይህንኑ ዓላማ ከግብ ሊያደርስ የሚችል መሆን እንደሚኖርበት በማሳሰብ የፌዴራል ስርዓቱን ማጎልበት የሚቻልባቸው ነጥቦች ላይ ሐሳብ አቅርበዋል።

ከሽግግሩ ወቅት ጀምሮ በተግባር 28 ዓመታትን፣ ሕገ መንግሥታዊ እውቅና ካገኘ ደግሞ 24 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ከፅንሰ ሃሳቡ ጀምሮ እስከ አተገባበሩ ድረስ በርካታ ትችቶች ይሰነዘሩበታል። የፌዴራል ሥርዓቱ የ50 ዓመት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አንኳር ጉዳይ ለመሆኑ ብዙዎችን ለሚያስማማው ‹የብሔሮች ጥያቄ› ምላሽ ሠጥቷል ብለው የሚያሞግሱት መኖራቸውን ያህል፣ በብሔሮች አብሮነት እና አገራዊ አንድነት ላይ ሥጋት ደቅኗል ብለው የሚተቹትም በርካታ መሆናቸው የሚታወቅ ነው።

በሥራ ላይ ያለውን የፌዴራል ሥርዓት በመተቸት የሚታወቁ ብዙዎቹ የፖለቲካ ኃይሎች ኢትዮጵያ የብሔር፣ የቋንቋ እና የሐይማኖት ብዝኀነት ያለባት አገር እንደመሆኗ መጠን፣ የፌዴራል ሥርዓትን መከተል እንደሚኖርባት ይስማማሉ። ሆኖም “የፌዴራል አወቃቀሩ ግን ብሔርን መሰረት ያደረገ ሊሆን አይገባውም” የሚል እርስ በራሱ የሚጣረስ አቋም ያንፀባርቃሉ። አለፍ ሲልም ብሔርን መሰረት ያደረገው ፌዴራሊዝም በ“መልክዓ ምድራዊ ፌዴራሊዝም” ሊተካ ይገባል የሚል አማራጭ ሐሳብ ያቀርባሉ። ትችቱም ሆነ አማራጭ ሐሳቡ በሥራ ላይ ያለው የፌዴራል ሥርዓት ያሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ ከሚል የመነጨ ቢሆንም፤ ችግሩን በጥልቀት የተነተነ እና ሊሆን የሚችል (plausible) አማራጭ ያቀረበ መሆኑ አጠራጣሪ ነው። አማራጭ ሐሳቡንም እርስ በእርሱ ተጣረሰ የሚያሰኙት ምክንያቶችም በርካታ ናቸው።

የፌዴራሊዝም አመክንዮ
የተለያዩ አገራት የተለያየ ዓላማን ለማሳካት ፌዴራላዊ ሥርዓትን ተግብረዋል። የፌዴራሊዝም ባለሙያዎች የተለያዩ የፌዴራል ሥርዓቶችን በተለዩ ምድቦች በመከፋፈል ጥናት እንደሚያደርጉ ቢታወቅም፤ አገራት የፌዴራል ሥርዓትን እንዲከተሉ ካደረጋቸው ምክንያቶች (rationales) አንፃር የተደረገ የፌዴራሊዝም ዓይነቶች ምደባ ግን እምብዛም አይታወቅም። ነገር ግን ከአመሰራረት አንፃር ኹለት የፌዴሬሽን ዓይነቶች እንዳሉ ይታወቃል።

ቀድመው ሉዓላዊ የነበሩ መንግሥታት ወደ አንድ በመምጣት የሚመሰርቱት የፌዴራል ሥርዓት “አሰባሳቢ” (coming-together) ፌዴሬሽን በመባል ሲታወቅ፤ በአንድ አገር ውስጥ ላሉ ራስ ገዝነትን የሚፈልጉ ቡድኖችን ወይም አካባቢዎችን የተወሰነ ሉዓላዊነት (autonomy) በመስጠት አገራዊ አንድነትን ለመጠበቅ የሚመሰረት የፌዴራሊዝም ዓይነት ደግሞ “አያያዥ” (holding-together) ፌዴሬሽን በመባል ይታወቃል።

እንደ አሜሪካ እና ስዊዘርላንድ ያሉ ፌዴሬሽኖች ቀድሞ ራሳቸውን የቻሉ መንግሥታት በአንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ውስጥ ለመኖር በመስማማታቸው ምክንያት የተፈጠሩ “አሰባሳቢ ፌዴሬሽኖች” ሲሆኑ፣ እንደ ጀርመን እና ሕንድ ያሉ አገሮች ደግሞ በውስጣቸው ላሉ አካባቢዎች የተገደበ ራስ ገዝነትን በመስጠት የተመሰረቱ “አያያዥ ፌዴሬሽኖች” ናቸው። የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት ራሱን እንደ አሰባሳቢ ፌዴሬሽን አድርጎ ቢያቀርብም ኢትዮጵያ ከነበራት የቀደመ ታሪክ አንፃር፤ የተለያዩ አከባቢዎች (ብሔሮች) ያነሱትን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ በሚል የተመሰረተ “አያያዥ ፌዴሬሽን” ነው ተብሎ የሚጠቀስ ነው።
ሆኖም እነዚህን “አያያዥ ፌዴሬሽኖች” እንዲመሰረቱ ያስገደደው ምክንያት (rationale) ተመሳሳይ አይደለም። እንደ ሕንድ፣ ቤልጅየም እና ናይጄሪያ ያሉ አገራት በዋናነት ብዝኀነትን ለማስተናገድ በሚል ዓላማ የፌዴራል ሥርዓትን የሚተገብሩ ቢሆኑም ሁሉም “አያያዥ ፌዴሬሽኖች” ብዝኀነትን ለማስተናገድ በሚል ዓላማ ተመስርተዋል ብሎ መደምደም አይቻልም። ለምሳሌ ያህል የጀርመንን የፌዴራል ሥርዓት ብዝኃነትን ለማስተናገድ ካለው ዓላማ ይልቅ ያልተማከለ አስተዳደርን ለመፍጠር ያለው ዓላማ የበለጠ ጎልቶ ስለሚታይ ፌዴሬሽኑ ብዝኃነትን ለማስተናገድ በሚል ዓላማ የተቋቋመ ነው ለማለት ይከብዳል።

የፌዴሬሽኑ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አሸናፊ የነበሩ ኃይሎች የናዚ አይነት አምባገነን መንግሥት በጀርመን ምድር እንዳያንሰራራ ለማድረግ ሥልጣንን ከማዕከላዊ መንግሥት ለማራቅ ወይም ለመቀነስ ያሳደሩት ግፊት ውጤት መሆኑ ይታመናል። ግፊቱ ከሌሎች አገራት የመጣ ቢሆንም፣ የአገሪቱ ፖለቲከኞች ግን አካባቢያው ውሳኔ ሰጪነትን፣ ያልተማከለ አስተዳደርን እና ሕዝባዊ ተሳትፎን የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ተጠቅመውበታል።

አገራት የፌዴራል ሥርዓትን እንዲከተሉ የሚያስገደዳቸው ምክንያት የፌዴሬሽኑ አባል መንግሥታት (ክልሎች) የሚዋቀሩበትን ሁኔታ ይወስናል። ብዝኀነትን ለማስተናገድ በሚል ዓላማ የሚተገበር የፌዴራል ሥርዓት ብዙኀነትን ለማስተናገድ የሚያስችለው ተቋማዊ አደረጃጀት ሊኖረው ይገባል። የቤልጅየም የፌዴራል ሥርዓት ፈረንሳይኛ እና የደች ቋንቋ የሚናገሩ ዜጎችን ብዝኀነት ለማስተናገድ ዋሉንያ እና ፍሌሚሽ የተባሉ ቋንቋን መሰረት ያደረጉ ክልሎችን ተፈጥረዋል። ኹለቱ ሕዝቦች አንድ ላይ የሚኖሩባት ብራሰልስ ከተማ ውስጥ ያለውን አብሮነት ለማስተናገድ ደግሞ ብራሰልስ ራሷን የቻለች የኹለት-ቋንቋ (bilingual) ክልል እንድትሆን ተደርጋለች። በተቃራኒው በጀርመን ፌዴራል ሥርዓት ከአስራ ስድስቱ ክልሎች ውስጥ ከተወሰኑት በስተቀር በታሪክ የሚታወቅ ክልላዊ ማንነት እና አንድ አይነት ባህል የነበራቸው አይደሉም። ሆኖም የፌዴራል ሥርዓቱ ከተመሰረተበት ዓላማ አንፃር ያልተማከለ አስተዳደር እና ውጤታማ አካባቢያዊ ዴሞክራሲ ለመገንባት የሚያስችለውን የፌዴራል መዋቅር እና አከላለል ዘርግቷል ማለት ይቻላል።

ይህ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ውስጥ መልክዓ ምድራዊ ፌዴራሊዝምን እንደ አማራጭ የሚያቀርቡ ኃይሎች ፌዴራሊዝም ለአገራችን የሚያስፈልገው ብዝኀነትን ለማስተናገድ መሆኑን ተስማምተው ሲያበቁ፤ የፌዴራሉ አባል ክልሎች አወቃቀር ብዝኀቱን ሊያስተናግድ በሚችል መልኩ መቀረፅ እንደሚኖርበት ይዘነጋሉ።
በአገራችን ያለው ብዝኀነት በበቂ ሁኔታ እውቅና እንዲሰጠው ካስፈለገ የቋንቋ እና የባሕል ልዩነቱ መስተናገድ የሚችልበት የመንግሥት አወቃቀር ማስፈለጉ አያጠራጥርም። በእርግጥ ፌዴራሊዝም ብዝኀነትን ማስተናገድ የሚችል የተሻለው የመንግሥት ሥርዓት እንጂ ብቸኛው አማራጭ ተደርጎ መወሰድ አይኖርበትም። ነገር ግን ከመነሻው ብዝኀነትን ለማስተናገድ በሚል የተቀረፀ የፌዴራል ሥርዓት ብዝኀነቱን የሚያስተናግድበት ተቋማዊ ቅርፅ ከሌለው ትርጉም አልባ መዋቅር ሆኖ ይቀራል።

“የመልክዓ ምድራዊ ፌዴራሊዝም” መነሻ
ጥቂት የማይባሉ ፖለቲከኞች በሥራ ላይ ያለውን የፌዴራል ሥርዓት ግድፈቶች ለማረም “መልክዓ ምድራዊ ፌዴራሊዝምን” እንደ አማራጭ ቢያቀርቡም በፌዴራሊዝም ጥናት እና ጽንሰ ሐሳብም ሆነ ሥርዓቱን በሚተገብሩት 25 አገራት ውስጥ “መልክዓ ምድራዊ ፌዴራሊዝም” የሚባል የፌዴሬሽን ዓይነት ፈፅሞ አይታወቅም። ሆኖም “መልክዓ ምድራዊ ፌዴራሊዝም” የሚለውን ሐረግን የሚጠቀሙ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ኃይሎች በዚህ ሐረግ ውስጥ ሊገልፁት የፈለጉት ፅንሰ ሐሳብ ግልፅ ነው።

መነሻ ሐሳቡም “ብሔርን መሰረት ያደረገው ፌዴራሊዝም የሕዝቦች አብሮነት እና አገራዊ አንድነት ላይ ሊፈጥረው የሚችለውን (የፈጠረውን) ተፅዕኖ ለማስቀረት፣ ብሔርን መሰረት ያላደረገ አወቃቀር መከተል ያስፈልጋል” የሚል ነው።አወቃቀሩ ምን ሊመስል ይገባል የሚለው ላይ ግን ተጨባጭ የሆነ መልስ ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች እምብዛም ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን)ን ከመሰሉ ቀኝ ዘመም የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ፕሮግራም ላይ ለመረዳት እንደሚቻለው፣ ፓርቲዎቹ ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ የመንግሥት አደረጃጀት ይኑራት በሚለው ላይ ተቃውሞ የላቸውም። ነገር ግን አሁን ያለው ብሔር ተኮር የፌዴራል አደረጃጀት በአዲስ መልክ እንዲዋቀር እንታገላል የሚል አቋም ይዘዋል። ምን ዓይነት አወቃቀር የሚለው ላይ ግን ጥቅል ደረጃዎችን/ሁኔታዎችን ከማስቀመጥ ባለፈ ይህ ነው የሚባል መዳረሻ ያለው እቅድ ያላቸው አይመስልም።

መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የሕዝብ አሰፋፈር፣ አስተዳደራዊ ምቹነት፣ ቋንቋ እና ባሕል እንዲሁም የሕዝብ ፍላጎት… ወዘተ የሚሉ ሐረጎችን በመዘርዘር የፌዴራል ሥርዓቱ እነዚህን መሰረት አድርጎ ይዋቀራል ሲሉ በፕሮግራማቸው ይገልፃሉ። ሆኖም የትኞቹ ሁኔታዎች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው በግልፅ አልተመላከተም፤ እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት ያስገባው አደረጃጀት የሚዋቀረው በምን አይነት ሕገ-መንግሥታዊ ሂደት መሆኑም በዝርዝር አልተገለፀም።

የሕዝብ ፍላጎት እና ዴሞክራሲያዊነት
ዴሞክራሲያዊነት እና የሕዝቦች ሉዓላዊነት የፌዴራሊዝም የማዕዘን ራሶች ከመሆናቸውም ባለፈ፣ እነዚህ ባልተከበሩበት ሁኔታ የፌዴራል ሥርዓት አለ ለማለት የማይደፍሩ የፌዴራዝም ጥናት ባለሙያዎች አሉ። ዴሞክራሲና እና የሕዝቦች ሉዓላዊነት ደግሞ የፌዴራል ሥርዓት አተገባበር ላይ ብቻ ሳይሆን የፌዴራል ሥርዓት አመሰራረት ላይም ጭምር እጅግ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ ቅድመ ሁኔታች ናቸው።

የፌዴራሉ አባል መንግሥታት (ክልሎች) የሚዋቀሩበት ቅርፅ የሕዝቦችን ፍላጎት እና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ከግምት ያስገባ መሆኑ ቀጣይነት ያለው አንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ ስለመመስረቱ ቀዳሚ ማረጋገጫ ነው። ሕዝቦች በፈለጉት እና ይወክለኛል ባሉት አካባቢያዊ አስተዳደር ሥር የመካተት እና የመተዳደር ምርጫቸው እስካልተከበረ ድረስ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ የሆነ የፌዴራል ሥርዓት ተግባራዊ ሆኗል ማለት ያስቸግራል።

ከላይ እንደማሳያ ባነሳናቸው እና በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራም ውስጥ የፌዴራል ሥርዓቱን እንደ አዲስ ለማዋቀር መሰረት ይሆናሉ ተብለው የተቀመጡ ሁኔታዎች ለዴሞክራሲ መርሆች እና ለሕዝብ ፍላጎት ቅድሚያ የመስጠታቸው ጉዳይ አጠያያቂ የሚሆነው እዚህ ላይ ነው። በኢሃን የፖለቲካ ፕሮግራም መሰረት የፌዴራል ሥርዓቱን እንደ አዲስ እንዲዋቀር የሚፈለገው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን፣ የሕዝብ አሰፋፈርን፣ አስተዳደራዊ ምቹነት እና የሕዝብ ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ ነው።

ሆኖም ከእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ የሕዝብ ፍላጎት በተለየ ቅድሚያ የሚሰጠው ስለመሆኑ ማረጋገገጫ ካለመሰጠቱም በላይ “የሕዝብ ፍላጎት” የሚለው ሐረግ በቅደም ተከተል ከሌሎቹ ሁኔታዎች በኋላ መቀመጡ በራሱ የሚያመላክተው አቋም አለ። በኢዜማ የፖለቲካ ፕሮግራም መሰረት ደግሞ የፌዴራል ሥርዓቱ እንደ አዲስ ለማዋቀር ከግምት ከሚገቡ ሁኔታዎች ዝርዝር ውስጥ ጭራሹኑ “የሕዝብ ፍላጎት” የሚል ሀረግ አይገኝም።

እንደማሳያ በወሰድናቸው ኹለቱ የፖለቲካ ፓርዎችም ሆነ በሌሎች ፓርቲዎች ፕሮግራም ውስጥ በተመሳሳይ መልኩ ሰፍሮ የሚገኘው የፌዴራል ሥርዓትን ለማዋቀር መሰረት ይሆናል የተባለ መርህ “አስተዳደራዊ ምቹነት” ነው። ይህም ክልሎች የሚዋቀሩት ማዕከላዊ መንግሥቱ ለአስተዳደር ይመቸኛል ባለው መንገድ እንጂ የዜጎችን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ እንዳይሆን የሚያደርግ መሆኑ ግልፅ ነው። መንግሥታት እነርሱ ለማስተዳደር በሚመቻቸው መልኩ ሸንሽነው የሚያዋቅሩት የፌዴራል ሥርዓት ገና ከመነሻው የሕዝቦችን ፍላጎት ያላከበረ፤ የዴሞክራሲ እና የፌዴራሊዝም መርሆችንም የጣሰ ነው።

መደምደሚያ
ብሔርን መሰረት አድርጎ የተዋቀረው የፌዴራል ሥርዓታችን አናሳዎች በክልል መዋቅሮች ሥር በቂ ፖለቲካዊ ውክልና እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ሥርዓት አለመገንባቱ፤ በሕዝቦች መካከል ተፎካካሪ ፍላጎቶች (competing interests) እንዲዳብሩ ማድረጉ፤ የግለሰብ መብቶች በብሔር ማዕቀፍ ሥር ብቻ የሚመለሱ ኹለተኛ ደረጃ መብቶች ሆነው እንዲቀመጡ ማድረጉ፤ በክልሎች መካከል ሰፊ የሆነ አለመመጣጠን መኖሩ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ክፍተቶች እንዳሉበት እሙን ነው።

ችግሮቹም እንዲያው በግርድፉ የመዋቅር ችግር ተብለው የሚታለፉ ብቻ ሳይሆኑ መሰረታዊ የሀገር ሕልውና፣ የሕዝቦች አብሮነት እና የሰብዓዊ መብቶች መረጋገጥ ላይ ሥጋት የሚጥሉም መሆናቸውም አጠያያቂ አይደለም። ሆኖም በሌሎች አገራት ተግባራዊ ተደርገው የብሔር ተኮር ፌዴራሊዝምን ደካማ ጎኖች መሙላት የቻሉ እንደ ‘የአናሳዎች ጥበቃ ሥርዓት’ (minority protection system)፤ ድንበር ተሻጋሪ ራስ ገዝነት (non-territorial autonomy) እንዲሁም ጠንካራ እና ተደጋጋፊ የበይነ-መንግሥታት ግንኙነት (inter-governmental relation) እና የመሳሰሉ አባሪ (complementary) ሥርዓቶችን በመዘርጋት የፌዴራል ሥርዓቱን ማጎልበት ይቻላል።

የፌዴራል ሥርዓቱን ማሻሻል እና ክልሎችን እንደ አዲስ ለማዋቀር መሞኮር እንዲሁ በደፈናው የተወገዘ ተግባር እንደሆነ ተደርጎ መቆጠር እንደማይገባው ግልጽ ነው። ሥርዓቱ እንደ አስፈላጊነቱ ራሱን እንዲያሻሽል (evolve እንዲያደርግ) ማድረግ የተሻለ እና ቅቡልነት ያለው ፌዴሬሽን ለመገንባት የሚያግዝ አዎንታዊ ሂደት መሆኑም ሊታመን ይገባል። ሆኖም ፌዴራሊዝሙ በመሰረታዊነት ያስፈለገበትን ብዝኀነትን የማስተናገድ አላማ ሊያሳካ በማይችል መልኩ የፌዴራል መዋቅሩ እንዲሻሻል ግፊት ማሳደር ሥርዓቱ ያሉበትን ዘርፈ ብዙ ችግሮን የሚፈታ ሳይሆን አዲስ ችግሮች ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ያስፈልጋል። ብሔርን መሰረት አድርጎ የተዋቀረው የፌዴራል ሥርዓት ያለበትን ክፍተቶች እና ያመጣቸውን ችግሮች ለመፍታት በሚል ሰበብ በሕዝቦች ፍላጎት ላይ ያልተመሰረት ‹መልክዓ ምድራዊ› የፌዴራሊዝም ሥርዓት ለመተግበር መሞከር ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው።

የፌዴራል ሥርዓቱን በዚህ መልኩ ለማሻሻል የሚደረግ ጥረት በሥራ ላይ ያለው የፌዴራል ሥርዓት ያለበትን የቅቡልነት ችግር የሚደግም እንጂ የሚቀርፍ እንደማይሆንም ሊታሰብበት ይገባል። ብዝኀነትን ለሚያስተናግድ የሚረዳ የፌዴራል ሥርዓት ያስፈልጋል ካሉ በኋላ ይህንኑ ለማድረግ የሚያስችል መዋቅር እንደሚያስፈልግ አለመቀበል ብዝኃነትን እውቅና ከመንፈግ የማይተናነስ ተግባር ነው። የፌዴራል ሥርዓቱን ለማሻሻል የሚደረጉ ሂደቶች እውነተኛ የሆነ የልሒቃን ድርድር የሚያስፈልጋቸው ከመሆናቸውም ባሻገር፣ በሕዝበ ውሳኔ አማካኝነት የሰፊው ሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎን የሚጠይቁ ናቸው። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ቀጣይነቱ የተረጋገጠ የፌዴራል ሥርዓት እና አገር መንግሥት መገንባት አስቸጋሪ ይሆናል።

ሚኒሊክ አሰፋ የሕግ ባለሙያና ተመራማሪ ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው minilikassefa@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here