“ድጎማውም አሁን ከባዶ ያልተናነሰ ነው፤ ገቢና ወጪያችን አልተመጣጠነም”- የታክሲ ሾፌሮች

0
738

የታለመ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ በሆኑ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ሲሰጥ ከነበረው የታለመ ድጎማ ላይ 50 በመቶ እንዲቀነስ መደረጉን ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር  አስታውቋል። 

ይህም በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ጭማሪ የሚያመጣ ቢሆንም የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ እስካሁን የታሰበ የታሪፍ ማሻሻያ እንደሌለ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

ከዚህ ቀደም ለታለመ ድጎማ ተጠቃሚዎች ለቤንዚን ሲሰጥ የነበረው በሊትር የ12 ብር ከ78 ሳንቲም ድጎማ ከጥር 1 ቀን 2016 እስከ መጋቢት 30 ቀን 2016 ድረስ ወደ በሊትር 6 ብር ከ39 ሳንቲም እንዲቀንስ መወሰኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

በተጨማሪም ለነጭ ናፍጣና ለኬሮሲን ሲሰጥ የነበረው በሊትር የ13 ብር ከ27 ሳንቲም ድጎማ በሊትር ወደ 6 ብር ከ63 ሳንቲም እንዲቀንስ ተወስኗል። 

የታለመ ድጎማ መቀነሱን ሚኒስቴሩ ይፋ ከማድረጉ ከቀናት በፊት የዋጋ ጭማሪ መደረጉን አሽከርካሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከዚህም ባለፈ የድጎማው መቀነስ የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ 77.65 ብር ሲሆን ለታለመ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚዎች ቀድሞ 12 ብር ከ78 ሳንቲም ሲቀነስላቸው በሊትር 65 ብር ገደማ ይገዙ ነበር።

አሁን ግን በድጎማ ቅነሳው መሰረት 6 ብር ከ39 ሳንቲም ተቀንሶ በ72 ብር ገደማ፤ ማለትም በሰባት ብር ጨምረው የሚገዙ ይሆናል። 

በተመሳሳይ ሁኔታ ከጥር 1 ቀን 2016 ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ለስድስት ወራት ለቤንዚን ተጠቃሚ አገር አቋራጭ አውቶብሶች፣ የከተማ አውቶብሶች እና ፐብሊክ ሰርቪሶች በሊትር ሲያገኙት ከነበረው የ22 ብር ከ36 ሳንቲም ድጎማ ወደ 19 ብር ከ16 ሳንቲም በሊትር መቀነሱ ታውቋል። ነጭ ናፍጣ እና ኬሮሲን ላይ በሊትር 23 ብር ከ21 ሳንቲም የነበረው ድጎማ አሁን 19 ብር ከ89 ሳንቲም ሆኗል።

ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን የገለጹ የታክሲ አሽከርካሪዎች “የምናገኘው ገቢ ከወጪው ጋር የማይመጣጠንም፤ በመሆኑም አገልግሎት ከምንሰጠው ጭማሪ ለመስራት ያስገድደናል” ብለው ድጎማውም ቢሆን የሚያደርግልን አስተዋጽኦ “ከባዶ አይተናነስም” ብለዋል።

የድጎማ መቀንስን ተከትሎ አዲስ ማለዳ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮን የታሰበ የታሪፍ ማሻሻያ ስለመኖሩ የጠየቀች ሲሆን የድጎማ ቅነሳውን ተከትሎ የሚደረግ የታሪፍ ማሻሸያ እስካሁን እንዳልታሰበ እና የሚደረግ ከሆነ ይፋ እንደሚያደርግ ታውቋል። 

የትራንስፖርት እጥረት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የታሪፍ ጭማሪ ታክሲ ተጠቃሚውን ማህበረሰብ ለችግር እየዳረገ መሆኑን ተከትሎ ይህ የድጎማ ቅነሳ ለታክሲ ተጠቃሚው ማህበረሰብ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሊሆንበት እንደሚችል አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች በሙሉ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል።

በከተማዋ በአሁኑ ወቅት የቤንዚን ዋጋ በሊትር 77.65 ብር ሲሆን በዕቃ በመቅዳት ውጪ እስከ 80 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑ ተመላክቷል። 

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የታለመ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ የሆኑ የህዝብ ትራንስፖርት  አገልግሎት ሰጪ ሾፌሮች እንደገለጹት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከማስታወቁ ከ5 ቀናት በፊት እንደተደረገ ተናግረዋል።

አክለውም በየጊዜው እየቀነሰ የመጣው ድጎማ ካለው የነዳጅ ዋጋ ጭማሬ ጋር እንዲሁም የማደያዎች ከታሪፍ በላይ መሸጥ ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው እና ኑሯቸውን ከእጅ ወደ አፍ እንዳደረገባቸውም ገልጸዋል።

በአንጻሩ የድጎማ ስርዓቱ ከሚፈቅደው አሠራር ውጭ በሆነ መንገድ ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ ከ3 ሺሕ 1 መቶ በላይ ተሽከርካሪዎች በጊዜያዊነት ከነዳጅ ድጎማው መታገዳቸውን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ማስታወቁ አይዘነጋም።

በተጨማሪም በኮንትራት ስራ እና ለተማሪ ሰርቪስ መሰል አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ከድጎማ ውጪ መሆናቸው ይታወቃል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here