ሶማሊያ የኢትዮጵያ መንግስትን በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንድትጠይቅ እንደግፋለን- የአረብ ሊግ

0
568

ኢትዮጵያ የዓረብ ሊግን መግለጫ ፈጽሞ አትቀበልም- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት መሻከር እና ውጥረት መባባስን ተከትሎ የተጠራው የአረብ ሊግ አስቸኳይ ጉባዔ የሶማሊያ ሉዓላዊነት ተጥሷል የሚል ጠንካራ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

አዲስ ማለዳ የተመለከተችው የአረብ ሊግ መግለጫ በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሊያ ጎን በመሰለፍ “ባዶ እና ተቀባይነት የሌለው ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ” ነው ሲሉ አውግዘውታል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኤክስ (የቀድሞ ትዊተር) ገጻቸው ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ አቋምን በፍጹም አትቀበልም በማለት አስፍረው አዲስ ማለዳ ተመልክታለች። 

አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እንደገለጹት “ኢትዮጵያ የአረብ ሊግን መግለጫ አጥብቃ ትቃወማለች። ኢትዮጵያ ከበርካታ የአረብ አገራት ጋር ጥሩ የሁለትዮሽ ግንኙነት የምታራምድ ቢሆንም የአረብ ሊግ ግን የጥቂቶችን ፍላጎት እያስፈፀመ ነው”።

የወቅቱ የአረብ ሊግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀ መንበር አገር የሆነችው የመን ባሰናዳችውና በበይነ መረብ አማካኝነት የተደረገው የአረብ ሊግ አስቸኳይ ጉባዔ ለሶማሊያ አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት ጥበቃ ጽኑ ድጋፍ ለማድረግ የተስማሙበትን አቋም ይፋ አድርገዋል።

በአገራቱ አቋም መሰረት የሶማሊያን ሉዓላዊነት ጥሶ የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሊያ ጎን ሆነው ውድቅ ማድረጋቸውን እንዲሁም የሶማሊያን ወቅታዊ የውስጥ ችግር እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቀመው የሚደረጉ ጥሰቶችን እንደሚያወግዙ አስታውቀዋል። 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ “በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እና ሉዓላዊነት ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግ ሙከራ ነው” ያሉት ይኸው መግለጫ የሶማሊያ ሪፐብሊክ መንግስት “የተጋረጠበትን የሉዓላዊነትና ጣልቃ ገብነት አደጋ” ለመቀልበስ የኢትዮጵያ መንግስትን በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲጠይቅ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል።

በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል በታህሳስ ወር መጨረሻ የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ በርካታ ድጋፍ እና ተቃውሞ እየገጠመው ሲሆን የተፈራረሙት አገራት አሁንም በስምምነቱ የተጣሰ ህግ እንደሌለ ደጋግመው በመግለጽ ሙግታቸውን ቀጥለዋል።

ይሁን እንጂ የሶማሊያ መንግስት ስምምነቱ በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው በማለት የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ አስተዳደሮችን እያወገዙ ይገኛሉ። 

የአሜሪካ መንግስት በዚሁ ሳምንት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት በቀጣናው የሚንቀሳቀሰውን እና “የአል ቃይዳ የሽብር ቡድን” አጋር ነው በሚባለው የአል ሸባብ ቡድን ላይ የሚወሰደውን እርምጃ እንደሚያደናቅፍ ስጋቷን አስታውቃለች።

የአረብ ሊግም ከዚህ በተመሳሳይ የተፈረመው ስምምነት ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም ማጣት እና አለመረጋጋት አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን አመላካች ነው በማለት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ የሚገኙ አባል የአረብ አገራት ለሶማሊያ ሉዓላዊነት መከበር ድጋፍ እንዲያደርጉ እና በተጨማሪም ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት እንዲታይ ግፊት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አስቸኳይ ጉባዔም በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውጥረት እንዲሁም በሱዳን ጦርነት ዙሪያ እንደሚመክር የሚጠበቅ ሲሆን የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት መሪ ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን የተቀናቃኛቸውን በጉባዔው መገኘት ተከትሎ ከኢጋድ ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧ አይዘነጋም።    

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here