ተመሳሳይ ፈተና ለተለያዩ የሥራ ዘርፎች ነው የተሰጠው- የከተማ አስተዳደሩ ሠራተኞች ቅሬታ ለአዲስ ማለዳ

0
1001

በርካታ የሥራ ቡድኖች እና ዘርፎች በስሩ ለሚገኙ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የወጣው ፈተና አንድ የሥራ ዘርፍን ብቻ ያማከለ ነው ሲሉ የከተማ አስተዳደሩ ሠራተኞች ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን የገለጹት ሠራተኞች እንደገለጹት በአንድ ተቋም ውስጥ የሒሳብ፣ የሕግ፣ የኢንፎርሜሽን እንዲሁም ሌሎች ባለሙያዎች ቢኖሩት ለሁሉም ተመሳሳይ ፈተና መስጠት አግባብ አይደለም ብለዋል።

አዲስ ማለዳ የፈተና ጥያቄዎቹን ለማየት ያደረገችው ሙከራ ከተፈታኞች በኩል ወረቀቱ እዛው በመሰብሰቡ ማሳየት አልቻልንም በማለታቸው አልተሳከም፤ ነገር ግን ፈተናው የሙያ ወይንም የባህሪ ጥያቄዎችን ሳይጨምር አምስት ጥያቄዎችን ብቻ የያዘ መሆኑን ተናግረዋል። 

ጥያቄዎቹ በስፋት “በግላዊነት የሚስተዋልበት ማለትም ‘ምን ቢሆን ይሻላል ትላለለህ?ወዘተ የሚል በግል ምልከታ ላይ የተመሠረተ ነው” በማለት ቅሬታቸውን የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኞች “ስለዚህ ውጤቱ ፈተናውን በሚያርመው ሰው የግል ምልከታ ላይ የተመሠረተ ነው የሚሆነው” ሲሉ ስጋታቸውን አመላክተዋል። 

በዚህም ዕውቀትና ብቃት ያላቸው ሠራተኞች ወድቀው ችሎታ የሌላቸው ሰዎች እያለፉ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸው “አንድ ፈተና አንድን ሠራተኛ በትክክል እንዲመዝን ከተፈለገ የሙያውን በርካታ ዘርፎች የዳሰሰና ሰፋ ያለ መሆነ ሲጠበቅበት በዘርፉ ከአምስት የማይበልጡ ጥያቄዎች ማውጣት ተገቢ አይደለም” ሲሉ ተጨማሪ ችግር ነው ያሉትን ጠቅሰዋል። 

ለአብነትም ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ፈተናው ሙሉ በሙሉ ስለ ግብይት መሆኑን ያነሱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የቁጠባ፣ የሕግ እና የሒሳብ ሠራተኞችም ከግብይት ባለሞያዎች ጋር ይሄንኑ ፈተና መፈተናቸው አመላክተዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ ለሚተገብረው ድልድል ሲባል ከ14 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሠራተኞችን ለፈተና እንደሚያስቀምጥ መግለጹ ይታወቃል።

ይኼን ተከትሎም እናት ፓርቲ ፈተናውን በመቃወም ሐሙስ ታህሳስ 11 ቀን 2016 ባወጣው መግለጫ “ፈተናው ሲቪል ሰርቪሱን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ተፈልጎ ሳይሆን በፖለቲካዊ ውሳኔ የመጣ በመሆኑ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም” ሲል ገልጾ ነበር።

ፓርቲው አክሎም መንግሥት እያደረገ የሚገኘው የፈተና እሩጫ የማይፈልጋቸውን ሠራተኞች ለማስወገድ በአንጻሩ ደግሞ የሚፈልጋቸውን ለመተካት ሆን ብሎ ያቀናበረው ስልት መሆኑን ለመገመት አያዳግትም በማለት መተቸቱም የሚታወስ ነው።

ይሁን እንጂ በሁለት ዙር የተሰጠውን ፈተና ውጤት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ጥር 20 ቀን 2016 ይፋ ባደረገው መሠረት ፈተናውን ከወሰዱ 3 ሺህ 861 ሠራተኞች ውስጥ 1 ሺህ 680 ወይንም 44 ነጥብ 39 በመቶ ብቻ የሚሆኑት ማለፋቸው ይታወቃል።

በመጀመሪያው ዙር ቀደም በነበረው ምዘና 10 ሺህ 257 ሠራተኞች በፈተናው መሳተፋቸውንና ከዚህም ውስጥ 5 ሺህ 95 ተፈታኞች ማለፋቸውን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል። በተጨማሪም ከ4 ሺህ 213 ተፈታኝ አመራሮች ውስጥ 1 ሺህ 422 ብቻ ማለፋቸው አይዘነጋም።

አዲስ ማለዳ በሠራተኞቹ የተነሳውን ቅሬታ አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ምላሽ ለማካተት ያደረገችው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። አዲስ ማለዳ የቢሮውን እና የከተማ አስተዳደሩን ምላሽ ለመቀበል በማንኛውም ጊዜ ዝግጁ ናት።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here