የጠቅላይ ሚኒስትሩ መሸለም በኢትዮጵያ ካለው ረሃብ አንጻር “ያልተጠበቀ” ነው ሲል ሂውማን ራይትስ ወቀሰ

0
523

የመንስታቱ ድርጅት የዓለም እርሻ ድርጅት (ፋኦ) “አግሪኮላ” የተባለውን ከፍተኛ ደረጃ ያለው ሽልማቱን ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መስጠቱን ሂዩማን ራይትስ ዋች “ያልተጠበቀ” ሲል ተችቶታል።

ጥር 19 ቀን 2016 በጣልያን በተካሄደ ስነ ስርዓት “ለምግብ ዋስትና፣ ጤናማ እና የተመጣጠነ የምግብ ልማት” ለማሳደግ ላደረጉት ጥረት በሚል እውቅናው መሰጠቱ አይዘነጋም።

“ኢትዮጵያ ካለችበት ሰብዓዊ ቀውስ እና ሰፊ የምግብ ዋስትና እጦት አንጻር ሽልማቱ አስገራሚ ነው” ሲልም መቀመጫውን ኤምሪካ ያደረገው የመብት ተሟጋች ድርጅት ገልጿል።

ሂውማን ራይትስ ዎች በትናንትናው ዕለት ባወጣው ጽሁፍ እና አዲስ ማለዳ እንደተመለከተችው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 ከተካሄደው የሰሜኑ ጦርነት በኃላ በአገሪቷ የሚገኙ የተለያዩ ስፍራዎች ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠው ይገኛሉ ሲልም ገልጿል።

እንዲሁም የሂዩማን ራይትስ ዋች መግለጫ እንዳለው የኢትዮጵያ አደጋ እና ሥራ ስጋት አመራር ኮሚሽን “እራሱ” በሰጠው መግለጫ እንኳን በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልል 4 ሚልየን የሚሆኑ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ማስታወቁን አስታውሷል።

የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በትላንትናው እለት በአማራ እና ትግራይ ክልል በረሃብ ሳቢያ 371 ሰዎች መሞታቸውን እና 21 ህጻንተ ህይወታቸው አልፎ መወለዳቸውን አረጋግጫለሁ ማለቱንም ኢዲስ ማለዳ ዘግባ ነበር።

በተመሳሳይም ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኃላም የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤይድ) ጨምሮ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ አቅራቢ አካላት በተለይም በትግራይ ክልል የሚቀርበው የሰብዓዊ እርዳታ “ከታለመለት ዓላማ ውጭ ለስርቆት ተዳርጓል” በሚል አቅርቦት ማቋረጣቸውም በተደራሽነት ላይ ክፍተት መፍጠሩ ተመላክቷል።

እንደ ሂዩማን ራይትስ ዋች ገለጻ አሁንም በትግራይ፣ በአፋር እና አማራ ክልል የምግብ ዋስትና እጦት እንደቀጠለ ነው ያለ ሲሆን በመንግስት ሃይሎችና ታጣቂዎች መካከል ያለው ግጭት ነገሮችን እያባባሰ ነው ሲል ገልጿል።

በትላንትናው ዕለት በአማራ እና ትግራይ ድርቅ እና ረሃብ ዙሪያ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) “ለችግሩ ተገቢው ትኩረት ባለመሰጠቱና አሁንም ድረስ በክልሉ የቀጠለ ግጭት በመኖሩ ምክንያት” ረሀቡ እንደቀጠለ የሚገኝ ሲሆን በእዚህ ረሀብ ምክንያት በርካታ ሰዎች እና እንስሳት እየሞቱ ይገኛሉ ማለቱ አይዘነጋም።

ግጭቶች ባሉበት ቦታ በርካታ ኢትዮጵያውያን መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ለሟሟላት “እየታገሉ” ነው ያለው ሂዩማን ራይትስ ዋች፤ የዓለም መሪዎች በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ መገንዘብ አለባቸው ሲልም ጥሪውን አቅርቧል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here