ንጹሀን ዜጎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት እየሞቱ ነው- ኢዜማ፣ ነእፓ እና ባልደራስ ለአዲስ ማለዳ

0
630

ባሳለፍነው ሳምንት የተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ ባለፈው ዓመት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት ማራዘሙን ተክትሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እንዲሁም የአሜሪካ ኤምባሲ በአዲስ አበባ እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስጋታቸውን መግለጻቸውን አዲስ ማለዳ መዘገቧ አይዘነጋም። 

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) የአደረጃጀት እና አቅም ግንባታ ኃላፊ ሙባረክ በሺድ “የሚሞቱት የንጹሀን ዜጎች ሞት ከተፋላሚ ኃይሎች በበለጠ ከፍ ብሎ ነው የሚታየው። ለዚህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል” ሲሉ ተናግረዋል። 

ነጻነት እኩልነት ፓርቲ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘምን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ዜጎች በሠላማዊ መንገድ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢ መልስ መስጠት የማይችሉ ስርዓቶች የህዝቦችን ፍላጎት እና ህገ መንግስታዊ መብት ለመጨፍለቅ የሚጠቀሙባቸው የአፈና እና የጭቆና መሳሪያዎች ናቸው” በማለት መግለጹን አዲስ ማለዳ ተምልክታለች።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘሙን ተከትሎ በአማራ ክልል እየትካሄደ ያለው ውጊያ እና ለአራት ወራት እንዲቀጥል የተወሰነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመጨረሻ ግብ “የክልሉን ነዋሪዎች ሰቆቃ ማራዘም እና ያለ ጠያቂ ሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን መከራ ማስቀጠል ነው” ሲሉ የመላው ኢትይጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ እናት ፓርቲ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዲሁም የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ በጋራ ባወጡት መግለጫም አስታውቀው ነበር። 

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ቃል አቀባይ በቃሉ አጥናፉ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መንግስት ንጹሀን ዜጎችን ጨቁኖ ለመያዝ እየተጠቀመበት ነው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የሕዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ እዩኤል ሰለሞን በበኩላቸው “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማይጣሱ ተብሎ የተደነገጉ መብቶች አሉ፤ ከእነሱም ውስጥ በህይወት የመኖር መብት ነው ይህ ደግሞ በግልጽ እየተጣሰ በመሆኑ ይህ ደግሞ ህግን መጣስ ነው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ “በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚቃጣ ጥቃት በአስቸኳይ ይቁም!” በማለት ዛሬ የካቲት 6 ቀን 2016 ባወጣው መግለጫ የተራዘመውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተቃውሟል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጀመሪያ ለማጽደቅ እንዲሁም ለማራዘም “በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት መጠን መጨመርን እና የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ማስጠበቅ” የሚሉ ምክንያቶች ቀርበዋል። 

አዲስ ማለዳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የሚነሳው ችግር አስፈላጊነቱ ላይ ነው ወይስ አተገባበሩ ላይ? በማለት ላነሳችው ጥያቄ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ቃል አቀባይ በቃሉ አጥናፉ “አዋጁ አተገባበሩም ላይ ሆነ አስፈላጊነቱ ላይ ችግር አለ፤ በመወያየት መፍታት የሚቻልን ነገር ወደ ጦርነት መውሰዱ ለንጹሀን ዜጎች ሞት መንስዔ ሆኗል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ደግሞ እያባባሰው ነው፤ በመሆኑም የዜጎቹን ሰብዓዊ መብት እየተጣሰበት ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። 

በተጨማሪ የባልደራስ ቃል አቀባይ “የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ያወጣው መግለጫ የቁጥር ስህተት” እንዳለው ገልጸው ፓርቲያቸው ባደረጉት ማጣራት ከ120 በላይ ንጹሀን ሰዎች መሞታቸውን “አረጋግጠናል” ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ትላንት የካቲት 5 ቀን 2016 ባወጣው መግለጫ “ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት የጠየቃቸው መረጃዎች እና ምላሽ ገና ያልደረሰ” መሆኑን እና “የተሟላ ምርመራ መደረጉ አስፈላጊነትን” ጠቅሶ፤ እስካሁን ድረስ በተደረገው ክትትል ማንነታቸው የተረጋገጠ ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎችን የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ምክንያት ከሕግ ውጭ ገድለዋል ብሏል። 

በተጨማሪም ኮሚሽኑ ከጥቆማዎችና ከልዩ ልዩ መረጃ ምንጮች ከተሰበሰቡት የሲቪል ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ የ45ቱ መሞት ቢረጋገጥም፤ “ነገር ግን የጉዳቱ መጠን ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ምክንያታዊ ግምት ለመውሰድ ተችሏል” ሲል ማሳሰቡን አዲስ ማለዳ መዘገቧ አይዘነጋም። 

የኢዜማ የሕዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ እዩኤል ሰለሞን በበኩላቸው አሁን ያሉት ችግሮች አብዛኞቹ መንግስት መወጣት ያለበትን ኃላፊነት ሳይወጣ በመቅረቱ የተፈጠሩ ናቸው ብለው “እነዚህን የማስቀረት ፍላጎት እና ኃላፊነት ቢኖረው ከጅምሩም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማስቀረት ይቻል ነበር” ብለዋል። 

በተመሳሳይ የነእፓ የአደረጃጀት እና አቅም ግንባታ ኃላፊ ሙባረክ በሺድ “ዋናው ነገር መዋጋት ወይም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እና ሕዝቡን ለማፈን መጠቀም ሳይሆን የህዝብን ፍላጎት ማወቅና ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን የሚያስፈልግ መፍትሄ መፈለጉ ላይ ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

“መንግስት ለዜጎቹ ጥበቃና ከለላ ካላደረገ መንግስት ለማለት አያስደፍርም፤ ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት በየትኛውም ቦታ በሠላም ወጥቶ መግባት አሳሳቢ ሆኗል። የዚህ ምክንያት ደግሞ መንግስት ተገቢውን ጥበቃ ለዜጎቹ ስለማያደርግ ነው” ያሉት ደግሞ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ቃል አቀባይ ናቸው። 

ኢዜማ በበኩሉ “ ለዜጎች ሽፋን ካለመስጠት ሳይሆን የበቀል ዓይነት እርምጃ ስለተወሰደ ነው። ለጽንፈኛ ቡድን ተባብራችውኋል በማለት በተወሰደ እርምጃ ነው ዜጎች የሞቱት” በማለት ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ አደረጃጀት እና አቅም ግንባታ ኃላፊ ደግሞ የዜጎችን ሠላም የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለ ሆኖ ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ መፍታት እና የህዝብን ጥያቄ በአግባቡ የመመለስ ጉዳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል። 

በተጨማሪም መንግስት ካለፉት አመሥት ዓመታት ጀምሮ “ከጦርነት ተላቆ አያውቅም ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላ፣ አፋር፣ አማራ ሁሉም ቦታ ጦርነት እና ግጭት አለ። በመሆኑም ጦርነቱ መቆም አለበት እንጂ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መኖር አለመኖሩ መፍትሄ አይደለም” ሲሉም የነእፓ አመራር የሆኑት ሙባረክ በሺድ ለሚዲያችን ገልጸዋል። 

ይሁን እንጂ በመንግስት ብቻ ሳይሆን ታጣቂ ኃይሎችም ለሠላም እውነተኛ ድርድር ለማድረግ ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል ያሉ ከአዲስ ማለዳ ዳር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሪሮች በትዕግስት እና በመነጋገር በጦርነቱ የሚጎዱትን ንጹሀን ዜጎች በማሰብ ኃላፊነት መውሰድ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here