በኢትዮጵያ ሰባተኛውን ግዙፍ ከተማ ነው የምንገነባው- ኦቪድ ሪልስቴት 

0
3096

 ባሳለፍነው ሳምንት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የ5 ሺህ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ውል የተፈራረመው ኦቪድ ሪል ስቴት ባዘጋጀው ‘ራዕይ 2024’ የተሰኘ ዐውደ ርዕይ በአንድ ቀን ከ1 ሺህ 500 በላይ ሰዎች የቤት ግዢ ውል መፈረማቸው ተገለጸ። 

ትላንት መጋቢት 1 ቀን 2016 በስካይላይት ኢትዮጵያ ሆቴል “አንድ ቀን፣ አንድ ህልም፣ አንድ ዕድል” በሚል በተደረገ መርሃ ግብር ድርጅቱ 1 ሺህ ቤቶችን ከ5 በመቶ በሚጀምር ቅድመ ክፍያ እስከ 40 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ በማድረግ ለአንድ ቀን ብቻ የሚቆይ ዕድል አመቻችቶ ነበረ። 

የኦቪድ ሪል ስቴት ዋና የሥራ ኃላፊ ዳንኤል አበበ ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት ድረስ ብቻ በቆየው መርሃ ግብር ዕውደ ርዕዩን ከጎበኙ ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ውስጥ ከ1 ሺህ 500 የሚበልጡ ሰዎች ቤት ለመግዛት ውል መፈረማቸውን ተናግረው “በጣም ከጠበቅነው በላይ ነው” ሲሉ አፈጻጸሙን ገልጸዋል። 

የሪል ስቴት ኩባንያው በተለያዩ አካባቢዎች የሚገነባቸውን መኖሪያ ቤቶች ስራ በይፋ ባስተዋወቀበት ዕለት በአጠቃላይ ከ63 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶችን የሚይዙ አምስት የተለያዩ የግንባታ ስራዎችን ይፋ አድርጓል። አዲስ ማለዳ ከኩባንያው ባገኘችው መረጃ መሰረት ‘ቡልቡላ’ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 60 ሺህ መኖሪያዎች የያዘ የከተማ ፕሮጀክት እየተከናወነ ሲሆን ግንባታው ሲጠናቀቅ 300 ሺህ ሰዎችን እንደሚይዝ ይገመታል። 

ይህም “በኢትዮጵያ ሰባተኛው ግዙፍ ከተማ ይሆናል፤ ሐዋሳ ከተማን በመከተል” ሲሉ የኦቪድ ግሩፕ አባል የሆነው ኦቪድ ክሊንግ አማካሪ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳምሶን መርዕድ ገልጸዋል። በተጨማሪም ይህ ስፍራ በብዛት ለሚገዙ ድርጅቶች ምቹ ነው የተባለ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሰራተኞቹ የ5 ሺህ ቤቶች ግዢ የፈጸመውም ከዚህ ፕሮጀክት ላይ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

በተለምዶ ጥይት ቤት በሚባለው አካባቢ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አጠገብ ከ1 ሺህ 700 በላይ ቤቶችን እንዲሁም አዲስ ቤተ መንግስት በተካተተበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጫካ ፕሮጀክት ጋር የተናበበ 1 ሺህ 900 ቤቶች የሚይዙ ፕሮጀክቶችም ይፋ ተደርገዋል። ኦቪድ ግሩፕ በርካታ የንግድ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን በስሩ የያዘ ኮርፖሬት ሆልዲንግ ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here