በኢትዮጵያ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መደበኛ ፓስፖርት ለማግኘት ከአገልግሎት አሰጣጡ ጀምሮ አሉ በተባሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን ፓስፖርት ፈላጊ ዜጎች ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጹ።
ከአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሐዋሳ፣ ጅማ፣ ድሬዳዋ፣ ጅግጂጋ፣ አሶሳ፣ ሆሳዕና እና ሌሎችም በርካታ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከሚሰጥባቸው ከተሞች ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን የገለጹ ሰዎች እንደተናገሩት ፓስፖርት ለማግኘት ከ8 ወር እስከ አንድ ዓመት ከ 4 ወር ድረስ የጠበቁ ሰዎች ይገኙበታል።
ለሁለት ዓመታት በጦርነት ውስጥ በቆየው የትግራይ ክልል ደግሞ አገልግሎቱ ከሰሜኑ ጦርነት እና ከፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት መልስ በመቀሌ ስራውን ባለመጀመሩ ፓስፖርት የሚፈልጉ ዜጎች ወደ ሌሎች ክልል ከተሞች መሄድ ግድ ሆኖባቸዋል።
ቅሬታዎቹን ተከትሎ አዲስ ማለዳ በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በተገኘችበት ወቅት በስፍራው ከሌሊቱ አስር ሰዓት ጀምሮ ሰዎች ወረፋ የሚይዙበት ሂደት መኖሩን ተመልክታለች። በሌላ በኩል አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት አሻራና ፎቶ ለመስጠት የሚሄዱ ሰዎች ብዙ ወረፋ የሌለው ሲሆን፤ ነገር ግን ፓስፖርት ለመውሰድ ያለው ወረፋ ከቀናት በላይ የሚወስድ መሆኑን ተገልጋዮች ይናገራሉ።
በአዲስ ማለዳ ምልከታ ወቅት በዕለቱ ስትመጣ ሶስተኛ ቀኗ መሆኑን የገለጸችው ዘቢባ ሃሰን “ለማሳደስ ብዬ ልጄን ይዤ በጠዋት ነው የመጣሁት። ሙሉ ቀን ተሰልፈን ውለን ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ወደ ቤታቹ ሂዱ አሉን። የማይሰሩ ከሆነ ለምን ሙሉ ቀን ያውሉናል” ስትል በምሬት ትናገራለች።
በተመሳሳይም የዘቢባን ሃሳብ የምትጋራው ሰላም የተባለች ሌላ ግለሰብ “ከምሳ ሰዓት በኋላ ጭራሽ አይሰሩም። ነገ ተመለሱ ማለት ነው ስራቸው” ብላ ከዓመታት በፊት በነበረው አሰራር ይኼ መጉላላት እንዳልነበር አስታውሳለሁ ትላለች።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ችግሮችን ለመፍታት እየሰራሁ ነው ሲል በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቢደመጥም፤ ተገልጋዮች ችግራቸው እየተፈታ አለመሆኑን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጹ ይስተዋላል።
እንዲሁም ከጓደኞቿ ጋር በተመሳሳይ ቀን በኦንላይን መመዝገባቸውን የገለጸችው ዓለም “በኋላ ክፍያውን እና አሻራና ፎቶም በተመሳሳይ ቀን ነው የሰጠነው። ከቀጠሮው ዕለት ወራት በኋላ የእነሱ ፓስፖርት ሲመጣ የኔ ግን አልመጣም” ትላለች። ወደ ኢሚግሬሽን ሄዳ የጠየቀች ቢሆንም “ዛሬ አይደልም” በሚል ተደጋጋሚ ቀጠሮ እየሰጧት መሆኑን ገልጻለች።
ፓስፖርት አዲስ ለማውጣትም ሆነ ለማሳደስ የተመዘገቡ ሰዎች ከተመዘገቡበት ቅደም ተከተል ይልቅ በመሀል ሌሎች የሚወስዱበት ሂደት በስፋት መኖሩ በርካቶች “ምክንያቱ ምንድነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
“መታወቂያ እና ፓስፖርት ለማውጣት ያለው ወረፋና እንግልት ሰልችቶኛል” የሚለው ሌላው ወጣት በስፍራው የሚገኙ ደላሎች በኢሚግሬሽን አካባቢ ለሚገኙ የፌደራል ፖሊስ አባላት የተወሰነ ብር እንዲሰጥና ቅድሚያ ማግኘት እንዲቻል ያመቻቻሉ ሲል ገልጿል።
በተመሳሳይም አዲስ ማለዳ በጎተራ ፓስፖርት ለመውሰድ በአዲስ መልኩ የተቋቋመው የኢምግሬሽን ዜግነት አገልግሎት መስጫ ተቋም ከጠዋት ጀምሮ ወረፋ በሚጠብቁ ሰዎች የተጨናነቀ መሆኑን ተመልክታለች።
በዚህም ወረፋው ብዙዎችን እንዳመረራቸው እና ወረፋ ጠብቀው ደርሷቸውም “ፓስፖርታችሁ እዚህ አልመጣም ወደ ኢሚግሬሽን ሂዱ” የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸውም ያነሳሉ። እዛ ሲሄዱ ደግሞ “እዛው ነው የምትወስዱት” በሚል ለተደጋጋሚ እንግልት መዳረጋቸውን እና ቅሬታቸውን ለማን አቤት ማለት እንዳለባችው ግራ እንደገባቸውም ገልጸዋል።

በክልል ከተሞች የሚገኙ ቅሬታ አቅራቢዎችም በስርዓት አለመደራጀት፣ ተገልጋይን ማጉላላት፣ ስድብ አለፍ ሲልም ዱላ የታከለበት አገልግሎት የተቋሙ መለያዎች ሆነዋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የመንግሥት አስተዳደር ለውጥ ከተደረገ ጀምሮ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት ተቋም ውስጥ የተለያዩ ለውጦች (ሪፎርም) የተደረገ ቢሆንም፣ አንዳንድ የተቋሙ ሠራተኞች በድለላ ሥራ የተሰማሩ አካላት ጋር በመመሳጠር የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
ለአብነትም የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ታምሩ ገምበታን ጨምሮ፤ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በጥቅምት ወር 2016 መታሰራቸው ይታወሳል።
አገልግሎቱን በዋና ዳይሬክተርነት ይመሩ የነበሩት ብሩህተስፋ ሙሉጌታ እና ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት ፍራኦል ጣፋ እንዲሁም ታምሩ ገምበታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሐምሌ 2015 መጀመሪያ ሳምንት አካባቢ ከኃላፊነት መንሳታቸውም አይዘነጋም።
በአዲስ አበባ ብሎም በክልል ከተሞች ፓስፖርት ለማውጣት በውጭ በኩል በሚገኙ ሕገ ወጥ ደላሎች በኢሚግሬሽን አገልግሎት ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞች ጋር በመተባበር ተገልጋዮች ከ50 ሺህ እስከ 70 ሺህ ብር ድረስ በማስከፈል ፓስፖርት ማግኘት የሚቻልበት ሂደት እንደነበር በተደጋጋሚ ተገልጿል።
አዲስ ማለዳ ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ቅሬታዎቹን የተመለከተ ምላሽ ለማካተት ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቢቀርም፤ ሆኖም ግን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ከብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያው ጋር በነበራቸው ቆይታ ባለፉት ስድስት ወራት ሰራተኞችን የማጥራት ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
በርካታ የተቋሙ ሠራተኞችን ከስራ ማገድ እንዲሁም በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉን አንስተው፤ በእነሱ ምትክ ከዚህ ቀደም የተሻለ የስራ አፈጻጸም አላቸው የሚባሉ ግለሰቦችን መተካታቸውን ጠቁመዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ አገልግሎቱ 24 ሰዓት የፓስፖርት ህትመትና የበይነ መረብ ምዝገባ አሠራር ዘርግቻለሁ፣ ሠራተኞችን አሰልጥኜ አሰማርቻለሁ ቢልም አሁንም በርካታ ተገልጋዮች በመስሪያ ቤቱ ደጅ ላይ ሲጉላሉ መመልከት እና ቅሬታዎች እንደቀጠሉ ናቸው።


