ኩሪፍቱ ሪዞርት በአርባ ምንጭ ከተማ አዲስ ሆቴል ሊገነባ ነዉ

0
1873

ኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ በአርባ ምንጭ ከተማ ሪዞርት ሆቴል ለመገንባት ከ30 ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ የሚሆኑ ሦስት ቦታዎች ቀርበውለት መረጣ በማካሔድ ላይ መሆኑ ተገለጸ።

ኩሪፍቱ በከተማው አዲስ ሆቴል ለመገንባት ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ፣ የሪዞርቱ ከፍተኛ አመራሮች የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ያቀረባቸውን የቦታ አማራጮች ለመመለክት በተገባደደው ሳምንት ወደ ስፍራው አምርተዋል። መረጣውን በማከናወንም በአጭር ጊዜ ዉስጥ ግንባታ እንደሚጀምር አስታውቀዋል።

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሰብስቤ ቡናቤ ለአዲስ ማለዳ እንዳረጋገጡት፣ አመራሮቹ እሁድ ታኅሳስ 19/2012 የመስክ ምልከታ የሚያደርጉ ሲሆን፣ ለግንባታ ተስማሚ የሚሉትንም ቦታ ከመረጡ በኋላ ከተማ አስተዳደሩ ቀጣይ ሥራዎችን ያከናውናል። ለዚህም የኩሪፍቱ ባለቤት ታዲዮስ በለጠን ጨምሮ የኩሪፍቱ ሪዞርት አምስት ልዑካን በነገው እለት አርባ ምንጭ እንደሚገኙ ሰብስቤ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

የኩሪፍቱ ቅርንጫፎችን የማስፋፋት ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም በሐዋሳ ከተማ ታስቦ ባይሳካም የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ግን ፕሮጀክቱን ለመቀበል እንደማያቅማማ የከተማዋ ከንቲባ ተናግረዋል።

ግንባታው እየተጠናቀቀ የሚገኘውን ሌዊ ሪዞርትን ጨምሮ በከተማዋ ውስጥ ያሉ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚካሔዱ ኢንቬስትመንቶች ቁጥር 200 የደረሰ ሲሆን፣ የእነዚህ የገንዘብ ግምት 3.2 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ከንቲባው ገልፀዋል።

ኩሪፍቱ ሪዞርት እና ስፓ በአዳማ፣ በባህርዳር እና በቢሾፍቱ ከተሞች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ በቢሾፍቱ ቅርንጫፉም በኢትዮጵያ የመጀመሪያዉን የውሀ ፓርክ አስገንብቷል።

የውሃ ፓርኩ 70 ሚሊዮን ብር የወሰደ ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜም አንድ ነጥብ ኹለት ሚሊዮን ሊትር ዉሃ ተሞልቷል። ከዛ በኃላ በቀን 400 ሺሕ ሊትር ዉሃ እንደሚፈጅ በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን መዘገቡ ይታወሳል።
ኩሪፈቱ ሆቴል ድርጅቱን በምሥራቅ አፍሪካ ለማስፋፋት ባለዉ እቅድ መሰረት በጅቡቲ ማዉቻ ደሴት ላይ ግንባታዉ እየተካሔደ ይገኛል። ማዉቻ ደሴት ለዋና፣ አሳ ማጥመጃ አመቺ ሲሆን፣ የጅቡቲ ሪዞርት 7 ሚሊዮን ብር ገደማ ይፈጃል ተብሏል። ግንባታዉ ሲጠናቀቀ ሙሉ የስፓ አገልግሎት፣ የባህር ምግቦች እና ዓለም ዐቀፍ ምግቦችን የሚያቀርብ ምግብ ቤት፣ ፊልሞችና ቴአትሮች የሚታዩበት አዳራሽ፤ የመዋኛ ገንዳ፣ የልጆች መጫወቻ ሜዳ፣ ፕሬዘደንሻል ክፍሎች እና 120 ክፍሎች የመሳሰሉት እንደሚኖሩት ታዉቋል። በጅቡቲ በሚገኘዉ በዚህ ደሴት የሚሠራዉ የኩሪፈቱ ሪዞርት በተያዘዉ እቅድ መሠረት ለ200 ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተገልጿል።
አርባ ምንጭ ከአዲስ አበባ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የምትገኝ ከተማ ስትሆን፣ በ40 ምንጮቿ ትጠራለች። አርባ ምንጭ በጫሞ እና አባያ ሐይቆች ዳርቻ የምትገኝ በመሆኗ ለፍራፍሬ፣ ለአሳ እርባታ እና ለቱሪስት መስህብ ተመራጭ ከተማ ናት።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here