የወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄውን ለፌዴሬሸን ምክር ቤት አቀረበ

0
525

የወላይታ ዞን ምክር ቤት ቅዳሜ ታኅሳስ 11/2012 ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በላከው አቤቱታ፣ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዞኑ ያስገባውን የክልልነት ጥያቄ እንዳይፈፀም እና ሕዝቡም በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን መብት በመንፈጉ ሕገ መንግሥቱ ተተርጉሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን ሕዝበ ውሳኔ ያድርጉልኝ ሲል ጠየቀ።

በዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አበበች አራሾ የተፈረመው ባለ ሰባት ገጽ አቤቱታ እንደሚያስረዳው፣ በታኅሳስ 10/ 2012 ለደቡብ ክልል ምክር ቤት የቀረበው የወላይታ ክልልን የመመስረት ጥያቄ ባለመፈፀሙ የደቡብ ክልል ተጠሪ የሆነበት አቤቱታ ለምክር ቤቱ ቀርቧል።

የወላይታ ዞን ምክር ቤት አቤቱታ እንዳመለከተው፣ የክልልነት ጥያቄው በሕገ መንግሥቱ መሰረት በአንድ ዓመት ውስጥ ሊመለስለት ቢገባም፣ በጥናት እንመልሳለን በሚል ጥያቄው እንዲጓተት መደረጉን ያትታል። ሕዝበ ውሳኔ ተደራጅቶለት በክልል እንዲዋቀር ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረለት ከሲዳማ ብሔር ጋር በተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረበው የወላይታ ብሔር፣ በቂ ምክንያት ሳይኖር ጥያቄው ለክልል ምክር ቤት ጉባኤ እንዳይቀርብ ተደርጓል ሲል በአቤቱታው ያብራራል።

ይህም የዴሞክራሲን ምህዳር የሚያጣብብ እና ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን እምነት የሚሸረሽር ነው ብሏል።
‹‹የፌዴሬሽን ምክር ቤት በብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መካከል ልዩነት ሳይፈጠር እኩል በመዳኘት የወላይታ ብሔርን የክልል ምስረታ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ የምንጠይቅ ሲሆን፣ የማይሆን ከሆነ ወደ አላስፈላጊ መስዋዕትነት የምንደርስ ይሆናል›› ሲል በአዲስ ማለዳ እጅ የገባው አቤቱታ ያስነብባል።

መንግሥት የሲዳማን ክልልነት ጥያቄ በወቅቱ ባለመፍታቱ ምክንያት የደረሰው እልቂት በወላይታ ብሔር ላይ እንዳይደርስ መንግሥት ጥንቃቄ የተሞላው አፋጣኝ መልስ ይስጠኝ ሲልም ምክር ቤቱ ጠይቋል።
በሕገ መንግሥቱ ላይ የክልል ምስረታ ጥያቄን የሚያብራራው አንቀጽ 47ን የጠቀሰው አቤቱታው፣ በዚህ አንቀጽ ላይ የተዘረዘሩትን አምስት መስፈርቶች የዞኑ ምክር ቤት ማሟላቱንም አስረድቷል።

የክልልነት ጥያቄንም መንግሥት ሲፈልግ የሚፈቅደው ወይም ሳይፈልግ የሚያነሳው ሳይሆን ሕዝቡ ራሱ የሚመሠርተው ነው ያለው የዞኑ ምክር ቤት፣ ‹‹በአንድ በኩል አንድ ሕዝብ የራሱን ክልል የመሆን መብት በመተግበሩ የዴሞክራሲ ምህዳሩ መስፋቱን ያሳያል እያለ መግለጫ እየሰጠ፣ በሌላ በኩል የሌላውን ሕዝብ ጥያቄ ማፈን ለዴሞክራሲ ምህዳር መጥበብ ምክንያት መሆን የለበትም›› ሲልም አትቷል።

የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ እና የሕግ መምህር ተከተል ላቤላ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት፣ የክልሉ ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን ጥሷል፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ይህንን የማረም እና የማውገዝ፣ በአገሪቱም የሕግ የበላይነት መኖሩን የማረጋገጥ እድል የሚሰጥ ይግባኝ ነው። ይህንንም ይጠቀማል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

‹‹የወላይታ ሕዝብ በጨዋነት እና በፍጹም ዴሞክራሲያዊነት ጥያቄውን ሲያቀርብ ቆይቷል። አሁንም ይህንን ይቀጥላል›› ያሉት ተከተል፣ ‹‹እንደ አንድ የብሔሩ ተወላጅም የዞኑ እንደራሴዎች የወከሉትን ሕዝብ ጥያቄ ይዘው መግፋታቸው አግባብ ነው ብዬ አምናለሁ›› ብለዋል። ‹‹የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተወከሉበት በመሆኑ ምክንያት፣ ይህንን ጥያቄ በሕጉ መሰረት ይመልሳል ብለን እናምናለን›› ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል እንዳረጋገጠችው፣ አቤቱታው ወደ ምክር ቤቱ ገቢ የተደረገ ሲሆን፣ በቀጣይ ለምክር ቤቱ ይቀርባል ተብሎ ይታሰባል።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here