የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በሕገ ወጥ ድርጊት የሚጠረጠሩ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደጀመረ አስታወቀ

0
382

ዓርብ ሐምሌ 05 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በትግራይ ክልል የተባባሰውን ሕገ ወጥ ድርጊቶች ለማስቆም እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ገለጸ።

አዲስ ማለዳ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በተመለከተችው አጭር መግለጫ፤ በክልሉ የተለያዩ ሕገ ወጥ ተግባራት ከጊዜ ወደጊዜ እየተበራከቱ በመምጣታቸው ምክንያት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መንግስት፤ መንግስትን የሚፈታተኑ እና የህዝቡን ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚከቱ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር በተለያዩ ኮሚቴዎች አማካይነት ሲያጣራ እንደቆየ ተገልጿል።

አብዛኛው ምርመራ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለማስቆም እና ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ስር ለማዋል ቅድመ ዝግጅት ማድረጉ በመግለጫው ተጠቁሟል።

በዚህም መሰረት በሕገ ወጥ የብረታ ብረት ዝርፊያና በመሳሰሉት ከባድ ወንጀሎች ላይ ከትላንት ሐምሌ 4 ቀን 2016 አንስቶ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ጀምሯል ተብሏል።

ሰኔ 22 ቀን 2016 የመቀሌ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት በ2016 ዓመት 11 ወራት ውስጥ 4 ሺህ 340 ወንጀሎች ተመዝግበው በዚህም 12 ሴቶች ሲገደሉ፣ 80 የአስገድዶ መደፈር፣ 1 ሺህ 953 የስርቆት፣ 583 የድብደባ፣ 178 የግድያ ሙከራ እንዲሁም 10 የጠለፋ ወንጀሎች መፈጸማቸውን እንዳስታወቀ አዲስ ማለዳ መዘገቧ አይዘነጋም። ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በመቀሌ ከተማ ከ170 በላይ የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ ሃይሎችን የማጠናከር ስራ ተሰርቷል ተብሏል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ትላንት በሰጠው መግለጫም ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረገው እንቅስቃሴ የመንግስት መዋቅሮች፣ የፀጥታ መዋቅርን ጨምሮ መላው ህዝቡ ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

በቅርቡ በክልሉ ዋና ከተማ እና ሌሎችም አካባቢዎች በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ግድያ እና አፈና ለማውገዝ ሰላማዊ ሰልፎች እንደተካሄዱ መዘገባችን አይዘነጋም።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here