የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በተለየ መንገድ ፖለቲካዊ ጫና እየደረሰብኝ ነው ሲል ወቅሷል፡፡
ለአንድ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ማብራሪያን የሰጠው ፓርቲው በታችኛውም ሆነ በላይኛው የፓርቲው መዋቅር ውስጥ ባሉ አመራሮች ላይ ግድያ፣አፈናና ከህግ ውጭ እስራት ተባብሶ ስለመቀጠሉ ነው የጠቆመው፡፡
ከዛም ባለፈ ፓርቲው የሚገለገልባቸው ተሸከርካሪዎችና መሰል የጽህፈት ቤት ንብረቶች ላይም ተደጋጋሚ ዘረፋ እየተፈጸመ ነው ሲልም ገልጿል፡፡
አገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ በእርግጥም ምክክር የሚያስፈልገው እንደሆነ እናምናለን ያለው ፓርቲው ይሁን እንጂ እንደምክክር ኮሚሽኑ ባሉና የመንግስት ጣልቃ ገብነት በስፋት በሚታይባቸው ተቋማት በኩል ዘላቂ መፍትሄ ይመጣል ብሎ እንደማያስብ አስታውቋል፡፡
በቀጣይ በሚኖሩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ ምቹ ፖለቲካዊ መደላደል መፍጠር ያስፈልጋል ያለው ፓርቲው ፤ የተዘጉ ጽህፈት ቤቶቻችን እንዲከፈቱ፤ የታሰሩ አባላቶቻችንም እንዲፈቱ ደጋግመን ብንጠይቅም መፍትሄ አላገኘንም ሲልም በማብራሪያው አንስቷል፡፡


