ቅዳሜ ሐምሌ 06 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ባለፈው ሳምንት ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ወደየቤቶቻቸው በመመለስ ላይ እያሉ በታጣቂዎች ከታገቱ ተማሪዎች የተወሰኑት የተለቀቁት የተጠየቀውን ክፍያ ከፍለው ነው ሲል አስታወቀ።
የደባርቅ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ ቤተሰቦቻቸው በመመለስ ላይ እያሉ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ገብረ ጉራቻ አካባቢ በታጠቁ አካላት መታገታቸው ይታወቃል።
ኢሰመጉ ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ “ከታገቱ ተማሪዎችም መካከል የተወሰኑት ተማሪዎች የተጠየቀዉን ክፍያ መክፈል በመቻላቸውና በተለያዩ ምክንያቶች ከአጋቾች ማስለቀቅ መቻሉን” ከሰበሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት እንደቻለ ገልጿል።
ትላንት ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ኮምኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሀይሉ አዱኛ፤ በሁለት ቀናት ኦፕሬሽን ውስጥ በመጀመሪያው ቀን 132 የሚሆኑትን እና ቡድኑ በፍጥነት ሊሰውራቸው ያላቻላቸውን ተማሪዎች ማስለቀቅ ሲቻል በሁለተኛው ቀን 28 የሚሆኑትን ማስለቀቅ ተችሏል ብለው ነበር።
በተጨማሪም አሁን ከሰባት ያልበለጡ ተማሪዎች በታጣቂ ቡድኑ ስር ይገኛሉ ተብሎ የሚገመት ሲሆን ሁሉንም ለማስለቀቅ ጥረት መቀጠሉን ለአዲስ ማለዳ መግለጻቸውን ዘግበን ነበር።
እንደመብቶች ጉባዔው ገለጻ ታጋቾች በተያዙበት ወቅት፤ አጋቾቹ ተማሪዎችን በቡድን በቡድን በማድረግ ወደ ተለያየ አቅጣጫ ይዘዋቸው የተንቀሳቀሱ በመሆኑ የተለቀቁ ተማሪዎች እየሰጡ ያለው እና አሁንም ድረስ ልጆቻቸው መታገታቸውን የሚገልጹ ቤተሰቦች መረጃ የሚያሳየው ተማሪዎች በነበሩበት ቡድን ውስጥ የተለቀቁ ተማሪዎችን ቁጥር ብቻ ነው ተብሏል።
በመሆኑም ከታገቱት አጠቃላይ ተማሪዎች ውስጥ ምን ያህል እደተለቀቁ የሚያሳይ አለመሆኑን እና ብዛት ያላቸው ተማሪዎች አሁንም በአጋቾች ታግተው እንደሚገኙ እና ለከፍተኛ እንግልትና ስቃይ መዳረጋቸውን ኢሰመጉ አስታውቋል። ይኹን እንጂ ኢሰመጉ ስለጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ምላሽ ለማግኘት “በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት” እንዳልተሳካ ተገልጿል።



