ኦፌኮ በአቶ በቀለ ገርባ ምትክ አቶ ሙላቱ ገመቹን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጎ መረጠ

0
327

ሰኞ ሐምሌ 08 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) በአቶ በቀለ ገርባ ቦታ አቶ ሙላቱ ገመቹን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጎ መምረጡን አስታወቀ፡፡

የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ አቶ በቀለ ገርባ ሃገር ውስጥ በነበሩበት ወቅት እርሳቸውም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ጫና ሲደርስባቸው እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

አቶ በቀለ ለፓርቲያቸውም ሆነ ለኦሮሞ ህዝብ ያላቸው ታማኝነት እስከ መጨረሻ አልተቀየረም ያሉት አቶ ጥሩነህ መንግስት በተደጋጋሚ በሚደርስባቸው ጫና ምክኒያት ሃገር ለቀው ለመሄድ ተገደዋል ብለዋል፡፡በተለይም ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ በሚያሳልፉበት ወቅት የግድያ ሙከራ ሲደረግባቸው እንደነበር አስረድተዋል፡፡

አቶ በቀለ በሰላማዊ መንገድ መታገልን የሚያስቀድሙ ቢሆንም በሃገሪቱ ስልጣን የያዘው አካል ግን ስለ ሰላማዊ ትግል ግድ የማሰጠው በመሆኑና ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባል ሆኖ ለመኖር ያለው እድል አናሳ በመሆኑ ከፓርቲው አመራርነት ለመልቀቅ በጠየቁት መሰረት ፓርቲው አምኖበት ጥያቂያቸውን እንደተቀበላቸው አቶ ጥሩነህ አስታውሰዋል፡፡

የኦፌኮ ዋና ጸሐፊ አክለውም አቶ በቀለ በደረሰባቸው ጫና ምክኒያት ከሃገር ከወጡ በኋላ ፓርቲያቸውንም ሆነ ህዝባቸውን በሚፈለገው ልክ በቅርበት ማገልገል የማይችሉ በመሆኑ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አምኖበት ጥያቄያቸውን በመቀበሉ፤ የእርሳቸው ቦታ ክፍት ሆኖ መቆየቱን አስረድተው በዚህ ቦታ ላይ አቶ ሙላቱ ገመቹ እንዲተኩ ተደርጓል ብለዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here