ሐምሌ 08 ቀን 2016(አዲስ ማለዳ)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ እና በአራት ኪሎ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች በኮሊደር ልማቱ ምክንያት ከቀድሞ የመኖሪያ መንደራቸው መነሳታቸው ይታወቃል፡፡
በመሆኑም ተለዋጭ ቤቶች እና ቦታዎችን በእጣ በማቅረብ በወጣላቸው እጣ መሰረት በለሚ ኩራ ክ/ከተማ ለልማት ተነሽዎቹ መኖሪያ ቦታን ያስረከበ ቢሆንም ነገር ግን ከፒያሳ እና አራት ኪሎ ተነስተው የመጡ ነዋሪዎች አስቀድም ሲኖሩበት ከነበረው ሁኔታ የከፋ ችግር ገጥሞናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ከፒያሳ እና አራት ኪሎ ተነስተው ለሚኩራ ክ/ከተማ ሳይት3 ጃርሶ አካባቢ በጋራ መኖሪያቤት ቦታ እንደተሰጣቸው የገለጹት ቅሬታ አቅራቢ ግለሰብ መሰረተ ልማት ያልተሟላበት ለመኖር ከባድ የሆነ አካባቢ ላይ እንድንሰፍር ሆነናል ብለዋል፡፡
አክለውም “መብራት፣ውሃ፣ቀረብ ያለ ጤና ተቋም እንዲሁም የተስተካከለ መንገድ የሌለው ከከተማ ተነስቶ ለመጣ እንኳን ቀርቶ ለማንም ሰው ለመኖር የሚከብድ ቦታ ነው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ማለዳ የነዋሪዎችን ቅሬታ በመያዝ የክ/ከተማውን ዋና ስራ አስፈጻሚ አነጋግራለች፤ “ቅሬታዎቹ ሙሉበሙሉ ሀሰት ነው ማለት አይቻልም” ሲሉም ምላሽ ሰተውናል፡፡


