ሐምሌ 11 ቀን 2016 ( አዲስ ማለዳ) የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የኮድ 2 ተሽከርካሪዎች በፈረቃ እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ አይደረግም አለ
ባለስልጣኑ የኮድ 2 ተሸከርካሪ የፈረቃ እንቅስቃሴ ወደፊት በጥናት የሚሆን እንጂ በቅርቡ ተግባራዊ የሚሆን አይደለም ብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ “ጠዋትና ማታ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ ኮድ 2 ተሽከርካሪዎች በፈረቃ እንዲንቀሳቀሱ ሊደረግ ነው” በሚል ርእስ በተቋሙ ባለሙያ ለሚዲያ የተሰጠው ማብራሪያ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አቋም አለመሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ “ጎዶሎ ቁጥር እና ሙሉ ቁጥር የኮድ 2 ተሽከርካሪዎችን በፈረቃ እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱንና የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን፥ በሁለት እና በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ በከተማው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኮድ 2 ተሽከርካሪዎች ወደ ፈረቃ እንዲገቡ ይደረጋል” ያሉት ከተቋሙ ያገኙትን መረጃ ተንተርሰው አለመሆኑ ተገልጿል፡፡
ጎዶሎ ቁጥር እና ሙሉ ቁጥር የኮድ 2 ተሽከርካሪዎችን በፈረቃ እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ ወደ ፊት ከመንግስት በሚሰጥ አቅጣጫ ተጠንቶ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ የሚደረግበት ሁኔታ እንደሌለ ተቋሙ አስታውቋል፡፡



