የ3 ወር ውዝፍ ደሞዝ አልተከፈለንም ያሉ የወላይታ ዞን የመንግስት ሰራተኞች ቁጣቸውን አሰሙ፡፡

👉የአካባቢው ባለስልጣናት በበኩላቸው ለደሞዝ የተያዘው በጀት ለአፈር ማዳበሪያ ግዢ ውሏል የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡

ሐምሌ 12 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የ 3 ወር ደሞዝ ስላልተከፈለን ቤተሰባችን አደጋ ላይ ወድቋል ሲሉ በወላይታ ዞን ሆቢቾ ወረዳ የሚያገለግሉ የመንግስት ሰራተኞች ናቸው ቁጣቸውን ያሰሙት፡፡

መሰረታዊ የሚባለውን መብታችንን ተነጥቀናል የሚሉት ሰራተኞቹ ከወርሃ ግንቦት አንስቶ ወርሃዊ ደሞዛችንን እያገኘን አይደለም፤ ይህም ኑሮን ከባድ አድርጎብናል በዚህ ዘመን እንኳን ያለደሞዝ በደሞዝም ህይወትን መምራት ከባድ ነው ሲሉ ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

ችግራችንን ከወረዳ እስከ ዞን ላሉ የመንግስት አመራሮች ብናሳውቅም መልስ ከመስጠት ይልቅ መሳለቂያ አድርገውናል የሚሉት ሰራተኞቹ ከዚህ ቀደም ለምን አይከፈለንም ብለው መብታቸውን የጠየቁ ሰራተኞችም ማስፈራሪያና ዛቻ ቤታቸው ድረስ በመሄድ ደርሶባቸዋል ሲሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት ያብራራሉ፡፡

ጉዳዩን ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመውሰድ ቅሬታችንን ብናቀርብም አስፈላጊውን በጀት ለዞን መድበናል ሄዳችሁ እዛ ጠይቁ ከማለት ውጪ መፍትሄ የሚሰጥ ምላሽን ማግኘት አልቻልንም ብለዋል፡፡

አሁንም ተገቢውን ምላሽ የሚመለከተው አካል እንዲሰጠን እንጠይቃለን ያሉ ሲሆን ገሚሱ የቤት ኪራይ መክፈል ባለመቻሉ በየጎዳናው ወድቋል የተቀሩትም ለከፋ ችግር ተዳርገዋል ሲሉም እሮሮአቸውን አሰምተዋል፡፡

የሆቢቻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ማእረጉ አስረስ በበኩላቸው በጀቱ የማዳበሪያ እዳ ላይ በመዋሉ ነው ደሞዝ መክፈል ያልተቻለው የሚል ምክንያትን አቅርበዋል፡፡

እንዴት ለመንግስት ሰራተኞች የተመደበን በጀት ለሌሎች የልማት ስራዎች ልታውሉት ቻላችሁ ስትል አዲስ ማለዳ ጥያቄ ያቀረበችላቸው አስተዳዳሪውም ከአዲሱ የክልሎች አደረጃጃት ጋር በተገናኘ የወረዳዎች ቁጥር በመብዛቱ ለማዳበሪያ የሚከፈለው ገንዘብ አዳጋች በመሆኑ ያለን አማራጭ ይህን በጀት መክፈል ነበር ሲሉም የሚያስተዳድሩት ወረዳ የተነሳበትን ቅሬታ ለመከላከል ሞክረዋል፡፡

ጉዳዩን በቶሎ ለመፍታት ንግግር እያደረግን ነው በተቻለ መጠን በፍጥነት ለመፍታት እንሞክራለን ብለዋል፡፡ነገር ግን እስከመቼ ለሚለው ግልጽ የሆነ ቀን ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚያገለግሉ መምህራን፣የአስተዳደር ሰራተኞችና መሰል ባለሙያዎች ከደሞዝ አከፋፈል ጋር በተያያዘ በተለያዩ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ቅሬታን እያሰሙ እንደሆነ ይታወቃል

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here