ሐምሌ 12 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ)ህወሃት ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ ላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ እረግጠው ወጥተዋል በሚል በአንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆችና አክቲቪስቶች ዘንድ ሲሰራጭ የነበረውን መረጃ አስተባበለ።
ሰሞኑን ህወሃት ባደረገው ስብሰባ አቶ ጌታቸውን ጨምሮ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባውን እረግጠው ወጥተዋል የሚሉ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶችና ተጠቃሚዎች ዘንድ በስፋት ሲዘዋወሩ ቆይተዋል።
ሆኖም የሕወሃት ቃል አቀባይ አማኑኤል አሰፋ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ ከጅምሩ እስከ ማጠናቀቂያው ድረስ ማንም መድረኩን ረግጦ የወጣ የለም ብለዋል።
ህወሓት 1 ሺህ 1 መቶ 11 ከፍተኛ አመራሮቹ በተገኙበት ባደረገው ስብሰባ የፓርቲው ዋና ውድቀት በስትራቴጂክ የመመራት ችግር መሆኑን መገምገሙን ቃል አቀባዩ የስብሰባውን ውጤት አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም ግምገማው የፓርቲውን ህልውና ለማስቀጠል የሚያስችል ውይይትና ምክክር ተካሂዶበታል ብለዋል።
ፓርቲው ህጋዊነቱን ለማስመለስ እየሰራ ነው ያሉት አቶ አማኑኤል 14ኛው የህወሓት ጉባኤ በያዝነው ሀምሌ ወር እንደሚካሄድም ገልጸዋል።



