

ሐምሌ 21 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ከማከሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎቹ ዋና ዋና የፖሊሲ ርምጃዎች መካከል አንዱ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓትን የሚመለከት ነው ሲል መንግስ ዛሬ እሁድ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
ይህ የውጭ ምንዛሬ ግብይት በገበያው አማካኝነት እንዲበየን የማድረግ ሂደት እንደሆነም ተገልጿል።
መንግሥት ” በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ማረጋገጥ በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ መዛባት ለማስተካከል ይረዳል ” ብሏል።
ከዚህ ባለፈም “ገቢና ወጪ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ዋጋ ከገበያ እውነታዎች ጋር እንዲጣጣም ያስችላል ፤ በክፍያ ሚዛን ላይ ያለውን አለመመጣጠን ለማስተካከል ይረዳል ” ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያወጡት ዘለግ ያለው መግለጫ ይጠቁሟል።
ሌላው ፥ በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ርምጃው የገንዘብ ፖሊሲ ማሕቀፉን ማዘመን ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል።
” የሦስት ዓመት የብሔራዊ ባንከ ስትራቴጂክ ዕቅድ ዝቅተኛ እና የተረጋጋ የዋጋ ንረት መኖሩን ማረጋገጥ ” መሆኑ የገለጸው መንግሥት ” ባንኩ ከንግድ ባንኮች ጋር በሚያደርገው የንግድ ግብይት በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት እንዲፈጠር ቅድሚያ ይሰጣል ” ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህንን የፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራ እንደጀመረ በይፋ አሳውቋል።
መንግስት በመግለጫው የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያው ሌላኛው ነው ያለ ሲሆን ዋና ትኩረቱም፦
– የመንግሥት ገቢን ማሳደግ፤ የመንግሥት ወጪንና የድጎማ ሥርዓትን ውጤታማ ማድረግ፣ በጡረታ ፈንድ ሥርዓቶች ላይ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን መተግበር፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማና ተወዳዳሪ ማድረግ እና የመንግሥት ብድር አስተዳደር ውጤታማና አዛላቂ እንዲሆን ማረጋገጥ ናቸውም ብሏል።
” ርምጃዎቹ የበጀት አስተዳደር ውጤታማነትን እና የመንግሥት ዕዳ ተጋላጭነትን ያሻሽላሉ ” ሲል የገለጸው መንግሥት ፥ ” በዚህ የተነሣ የልማት ፋይናንስ አማራጮቻችን ይሰፋሉ። ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶቻችንም በሀገር ውስጥ ዐቅም ለማሳካት ምቹ መደላድል ይፈጥራሉ ” ብሏል።
ሌላው እርምጃ የልማት ፋይናንስ ዕድሎች እና የመንግሥት ዕዳ አስታዳደር ማሻሻያ ናቸው ያለው
መንግሥት ” ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ጋር በተደረገው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ከተለያዩ አበዳሪዎች ጋር በመነጋገር ከፍተኛ የዕዳ ማሻሻያ ርምጃዎችን ለመውሰድ እየተሠራ ነው ” ብሏል።
” በሌላ በኩል ይህ የፖሊሲ ማሻሻያ ፕሮግራም ኢትዮጵያ አዳዲስ የልማት ፋይናንስ አቅርቦት በተለይም ከዓለም ባንከ፣ ከሌሎች የልማት ፋይናንስ አቅራቢ ባንኮች እና ከሁለትዮሽ አበዳሪ ድርጅቶች እንድታገኝ መንገድ ይከፍታል ” ሲል ገልጿል።
” በዚህም በአጠቃላይ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ትግበራ መሠረት በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ብዙ ቢልዮን ዶላር ኢትዮጵያ ታገኛለች ” ሲል ዛሬ ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።


