ሐምሌ 23 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፣ ነጻነትና እኩልነት እንዲሁም የሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርዓት አስመልክቶ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ፓርቲዎቹ በቆይታቸው ውሳኔው እንደ ሀገር የታመመው ኢኮኖሚ ላይ ተጨማሪ ጉዳትን የሚያስከትል እና ተራዛሚ ቀውስን የሚያዋልድ ነው ብለዋል ፡፡
የአሁኑ ውሳኔ የማህበረሰቡን ኑሮ በተለይም በእታችኛው የኢኮኖሚ ደረጃ የሚገኘውን የማህበረሰብ ክፍል የሚያደቅ ነው ሲሉም ነው አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ የሰጡት፡፡
በአገር ደረጃ እንደዚህ አይነት ተራዛሚ ቀውስን የሚያዋልዱ የፖሊሲ እርምጃዎች ከመወሰናቸው በፊት በቂ የሚባል ውይይት ቢደረግ የተሸለ ነበር ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ይህን ለማድርግ ግን መንግስት ፍቃደኝነቱን አላሳየም ሲሉ ወቀሰዋል፡፡
ይህ ደግሞ አገሪቷን እንደ ግል ንብረት ከመቁጠር የሚመነጭ እና በማን አለብኝነት የሚወሰን ውሳኔ ነው ሲሉ ውሳኔውን ተቃውመዋል፡፡
የፓርቲዎቹ አመራሮች የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በጦርነት በደቀቀበትና በጸጥታ ችግሮች የተነሳ በተቀዛቀዘበት ብሎም በቂ የውጭ ምንዛሬ ክምችት በሌለበት በዚህ ወቅት እንዲህ አይነት እርምጃዎች መወሰዳቸው መጪውን ጊዜ አስፈሪ ያደርገዋልም ነው ያሉት፡፡
መንግሥት በበኩሉ” በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ማረጋገጥ በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ መዛባት ለማስተካከል ይረዳል ” ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡



