ዕረቡ ሐምሌ 24 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ ለሚያቀርቡ አምራቾች እና አቅራቢዎች ክፍያ የሚፈጸመው በሚያወጣው የውጭ ምንዛሬ ተመን ተሰልቶ መሆኑን አስታውቋል።
የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ የሚመራ መደረጉን ተከትሎ ብሔራዊ ባንክ በወርቅ መግዣ ላይ አዲሱን አሰራር ተግባራዊ እንደሚያደርግ የገለጸ ሲሆን ለማንኛውም ወርቅ አቅራቢ ክፍያ የሚፈጸመዉ የእለቱን ዓለም ዓቀፍ የወርቅ ዋጋ በእለቱ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣዉ የውጭ ምንዛሪ ተመን ተባዝቶ ይሆናል ሲልም ነው በማብራሪያው የጠቆመው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ተመን በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወሰንበት የገበያ ስርአት መሸጋገሩ ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ማስታወቁ ይታወቃል፡፡
ላለፉት ጊዚያት እንደ ወርቅ እና ብር ያሉትን የከበሩ ማዕድናት የመግዛት እና የመሸጥ ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው ብሄራዊ ባንኩ በዓለም የወርቅ ዋጋ ላይ ማበረታቻዎችን በማከል ወርቅን ከአምራቾች እና ከአቅራቢዎች ሲገዛ መቆየቱ የሚታወስ ነው።



