በመርካቶ አካባቢ አንዳንድ ሱቆች እየተዘጉ መሆኑ ተሰማ 

0
1894

ዕረቡ ሐምሌ 24 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያስታወቀውን የውጭ ምንዛሬ የዋጋ ማሻሻያን ተከትሎ ከትናንት ሐምሌ 23 ቀን 2016 ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች እና ሱቆች በእቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሬ ታይቷል፡፡

ይህን ጉዳይ ተከትሎ በመርካቶ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች አዲስ ማለዳ ባደረገችው ቅኝት በተለያዩ ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሬ እንዳለ ተመልክታለች፡፡

በመሆኑም በመርካቶ አካባቢ አንዳንድ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን እንደዘጉ እንዲሁም የተለያዩ እቃዎችን በማሸሽ እና የለም በማለት የዋጋ ጭማሬውን እያባባሱት እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ሰምታለች፡፡

ይህን ተግባር የሚፈጽሙት የጅምላ አከፋፋዮች በመሆናቸው ሳይፈልጉ በሁኔታዎች አስገዳጅነት የዋጋ ጭማሬ ለማድረግ እየተገደዱ እንደሆነ የሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴዎች ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከ8 መቶ እስከ 9 መቶ ሲሸጥ የነበረ የምግብ ዘይት በአሁን ሰአት 1ሺ500 ብር እንዲሁም ሽንኩርት ቀድሞ ከነበረው 90 ብር 150 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑን ነጋዴዎች ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ የመኪና መለዋወጫ እቃ ከዚህ ቀደም ከነበረበት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ተመን በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወሰንበት የገበያ ስርአት መሸጋገሩ ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ማስታወቁ የሚታወስ ቢሆንም በሁለት ቀን ውስጥ በእቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት እየተስተዋለ ይገኛል፡፡

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎችም “ከወዲሁ የተስተካከለ የዋጋ ተመን እና ደንብ የማይተገበር ከሆነ ጭማሬ በሚያስፈልገውም በማያስፈልገውም እቃ ላይ ዋጋ እየጨመሩ የነጋዴ መጫወቻ መሆናችን ነው” ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በየሱቃቸው የሚገኘውን እቃ እየደበቁ የለም በማለት ሰው ሲቸገር በተባለው ዋጋ ይገዛል በማለት ገና ካሁኑ ገበያው ሌላ መልክ እየያዘነው ተገቢው እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ሲሉ አቅርበዋል፡፡

ከማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎቹ ዋና ዋና የፖሊሲ እርምጃዎች መካከል አንዱ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓትን የሚመለከት ነው ሲል መንግስ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

ይህ የውጭ ምንዛሬ ግብይት በገበያው አማካኝነት እንዲበየን የማድረግ ሂደት መንግሥት ” በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ማረጋገጥ በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ መዛባት ለማስተካከል ይረዳል ” ማለቱን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here