ሐሙስ ሐምሌ 26 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ መንግስት 1ሺህ 500 ብር የሚከፈላቸው ሰራተኞችን ደመወዝ በ300 ፐርሰንት ሊጨምር እንደሆነ እና ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ እንደመደበ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታውቀዋል፡፡
በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚቀርበው ተጨማሪ በጀት የሚካተተው የደመወዝ ጭማሪ በዋናነት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የመንግስት ሰራተኞችን የሚመለከት እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ተሿሚዎች ብዙ ላያገኙ ይችላሉ” ብለዋል።
ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ከፌደራል መንግስት ባለስልጣናት እና ከግል ባንክ ፕሬዝዳንቶች ጋር በተደረገ ውይይት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደመወዝ ጭማሪን ጉዳይ ያነሱት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተተገበረው የኢኮኖሚ ማሻሻያ “የሚጎዱ ሰዎች” መኖራቸውን ያመኑ ሲሆን ተጽዕኖውን ለመቋቋም ለሚያደርገው የደመወዝ ጭማሪ 90 ቢሊዮን ብር እንዳስፈለገም ጠቅሰዋል።



