አርብ 26 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) “ከፋኖ ሃይሎች ጋር የሚደረገው ንግግር ትልቅ ፖለቲካዊ አጀንዳን ያነገበ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” ሲል የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ገለጸ::
የአማራ ህዝብ ከ50 ሚሊየን በላይ እንደሆነ ይታወቃል የዚህን ህዝብ አሁናዊ የፖለቲካ ችግር ለመፍታት መደራደር ዋነኛ ግብ መሆንም ይኖርበታል ያሉት የካውንስሉ ሰብሳቢ አቶ ያየህይራድ በለጠ በዚህ ሂደት ውስጥ በፋኖ ሃይሎች በኩል የሚነሱ ቅድመሁኔታዎችን እንደተራ አጀንዳ መቁጠርም አግባብነት የለውም ብለዋል፡፡
ሰብሳቢው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአብዛኛው የአማራ ክልል አካባቢዎች ከሚገኙ የታጣቂ ቡድኑ አመራሮች ጋር መነጋገራቸውን ገልጸው ሁሉም የየራሳቸውን ሃሳብ አንጸባርቀውልኛል ብለዋል፡፡
አንዳንድ አመራሮች በግለሰብ ደረጃ በቶሎ መደራደርን ይፈልጋሉ አንዳንዶች ደግሞ በርከት ያሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀምጣሉ ያሉት ሃላፊው እነዚህ ሃይሎች በአንድነት የሚንቀሳቀሱበትን መንገድ መርጠው ቢጓዙ በድርድር ሂደቱ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ነው የጠቆሙት፡፡
ነገር ግን ሰብሳቢው ከየትኛው አመራር ጋር ተገናኝተው ስለማውራታቸው ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትናትናው እለት በነበራቸው ምጣኔ ሃብበታዊ ማብራሪያ ላይም መንግስታቸው ሸኔ ብሎ ከሚጠራውም ሆነ በአማራ ክልል ከሚገኘው የፋኖ ሃይል ጋር ንግግር መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
ለመሆኑ መንግስት በዚህ መልክ ንግግር እያደረኩኝ ነው ሲል የሚሰጣቸው ማብራሪያዎች በካውንስሉ ስራ ላይ ተጽእኖ አያሳድርም ወይ ስትል አዲስ ማለዳ ጥያቄ ያቀረበችላቸው ሰብሳቢው በመንግስት በኩል የተካሄደው ርቀት የሚበረታታ ሆኖ አግኝተነዋል በማለትም ነው የገለጹት፡፡
በአማራ ክልል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በሚል ከወራት በፊት የተቋቋመው የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል የገለልተኝነት፣የተገቢነትና መሰል ጥያቄዎች በበርካቶች ዘንድ ይቀርብበታል፡፡



