ማክሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ)ፍርድ ቤቱ አቶ ታዬ ደንደአ ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች መካከል በ1ኛ እና በ2ኛ ክስ ነጻ የተባሉ ሲሆን ከጦር መሳሪያ ጋር ተያይዞ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል፡፡
ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ-መንግሥትና በሕገ-መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ነው።
የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በአቶ ታዬ ደንደአ ላይ ሦስት ክሶችን አቅርቦ ነበር።
ዛሬ በዋለው ችሎት በነበረው ዝርዝር ክስ ላይም ተከሳሹ ሚኒስትር ዴዔታ ሆነው ሲሠሩ የሀገር፣ የመንግሥትና የሕዝብን ደኅንነት ማስጠበቅ ብሎም ማረጋገጥ ሲገባቸው፤ ይህን ወደጎን በመተው የሽብር ቡድኖችና ፀረሰላም ኃይሎችን የሚደግፉ ፕሮፓጋንዳ መልዕክቶችን በስማቸው በከፈቱት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ሲያስተላልፉ ነበር የሚለው ይገኝበታል፡፡
በተጨማሪም ፈቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ መሳሪያ፣ ሁለት የክላሽንኮቭ ካዝና እና 60 ተተኳሽ ጥይት ተገኝቶባቸዋል የሚል ክስ መቅረቡ ይታወሳል።
ክሱ ከደረሳቸው በኋላም ተከሳሹ “የጻፍኩት ጽሑፍ ፕሮፓጋንዳ አይደለም፤ ወንጀል አልፈጸምኩም” ሲሉ የዕምነት ክህደት ቃል መስጠታቸውን ተከትሎ፤ ዐቃቤ ሕግ ምስክር እንዲሰማ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የምስክር ጭብጥ በችሎት ካስመዘገበ በኋላ የሁለት ግለሰቦች የምስክር ቃላቸውን አሰምቶ ነበር።
ፍርድ ቤቱም የተሰሙ ምስክሮችን ቃልና በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ተላልፈዋል የተባሉ የፕሮፓጋንዳ መልዕክቶችን የያዙ የሠነድ ማስረጃዎችን መርምሮ ዛሬ ብይን ሰጥቷል።
በዚህም ተመሳሳይነት ያላቸውን ንግግሮችና ጽሑፎች ዐቃቤ ሕግ የተለያየ ክስ አድርጎ 1ኛ እና 2ኛ ብሎ ማቅረቡ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 61ን ያላገናዘበ ነው በሚል በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡
ይሁን እንጂ በመኖሪያ ቤታቸው በተደረገው ብርበራ የጦር መሳሪያ መገኘቱ በዐቃቤ ሕግ ማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑን በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ ክሱን እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡
ከብይኑ በኋላም ተከሳሹ አቶ ታዬ እንዲከላከሉ በተበየነበት 3ኛ ክስ የዋስትና መብት ተፈቅዶ በውጭ ሆነው ጉዳዩን ለመከታተል እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።
ዐቃቤ ሕግም አቶ ታዬ የተባሉበት ድንጋጌ ከ8 ዓመት እስከ 20 ዓመት የሚያስቀጣ ድንጋጌ በመሆኑና የዋስትና ግዴታቸውን አክብረው ላይቀርቡ ይችላለ በማለት የዋስትና መቃወሚያ መከራከሪያ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የዋስትና ጥያቄውን መርምሮ ከሠዓት በኋላ በነበረ ቀጠሮ ተከሳሹ በዋስ ቢወጡ የሕግ ግዴታቸውን አክብረው ሊቀርቡ አይችሉም የሚለውን ግምት በመያዝ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡
ፍርድ ቤቱ አቶ ታዬ ደንደኣ ተከላከሉ በተባሉበት 3ኛ ክስ ላይ የመከላከያ ማስረጃ ለመጠባበቅ ለጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡



