ማክሰኞ ነሐሴ 01 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በትግራይ ማእከላዊ ዞን ዓድዋ ወረዳ የመሬት መደርመስ አደጋ የደረሰ ሲሆን የመሬት መደርመስ አደጋው በሰው ህይወት ያደረሰው ጉዳት ባይኖርም የእህል አዝርእት ሙሉ በሙሉ ማውደሙን አዲስ ማለዳ ሰምታለች፡፡
የመሬት መደርመስ አደጋው ያጋጠመው ሀምሌ 29ቀን2016 ዓ.ም በዓድዋ ወረዳ በይሓ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነው፡፡
የወረዳው የቁጠባ ዘርፍ ፅ/ ቤት ” በአደጋው የ21 አርሶ አደሮች የተዘራ እህል ሙሉ በሙሉ ወድሟል “ማለቱን አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ሰምታለች፡፡
” ከአሁን በፊት በትግራይ ያልተለመደ የመሬት የመደርመስ አደጋ አሁን አሁን መታየት ጀምሯል ” ያለው ፅ/ቤቱ ፤ አርሶ አደሩ የክረምቱን ሀያልነት ከግምት ያስገባ ሁሉን አቀፍ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሲል አሳስቧል።
ዘንድሮ በትግራይ ክልል ያለው ኃይለኛ ክረምት በንብረትና በእንስሳት አደጋ በማደረስ ላይ እንደሚገኝ እና ባሳለፍነው ሳምንት በክልሉ የራያ ጨርጨር ወረዳ ዝናብ ያስከተለው ኃይለኛ ጎርፍ በ106 የቤት እንስሳትና በ11 ሄክታር የእርሻ መሬት ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አዲስ ማለዳ ሰምታለች፡፡
በጎርፉ 91 እንስሳት ሲወሰዱ 15 ቱ የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው በ11 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ እህል ከጥቅም ውጭ ሆኗል ።



