ረቡዕ ነሐሴ 01 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ከወራት በፊት የተገደሉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ወንድም እና ከግድያው ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ 11 ሰዎች እንዲፈቱ አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠይቋል።
የመንግስት ባለስልጣናት ከአቶ በቴ ግድያ ጋር በተያያዘ ክስ ሳይመሰረትባቸው ታስረው የሚገኙ ሰዎችን በአስቸኳይ እንዲፈቱ ሲል የመብት ተሟጋች ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል ።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ጉዳዮች ኦፊሰር የነበሩት አቶ በቴ ኡርጌሳ ሚያዚያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ሌሊት በኦሮሚያ ክልል መቂ ከተማ የፊጥኝ ታስረው በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት ተመተው መገደላቸውን ተከትሎ ፖሊስ የበቴን ወንድም ሚሎ ኡርጌሳን ጨምሮ 13 ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የገለጸው ሂዩማን ራይትስ ዎች አብዛኞቹ እስካሁን በእስር ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።
መንግስት የአቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ ጉዳይ አስፈላጊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለወንጀል ምርመራው ዓለም አቀፍ እርዳታ መጠየቅ አለበት ሲልም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ደረጅቱ አስገንዝቧል።
የፖለቲከኛውን ግድያ ተከትሎም ፓርቲያቸው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ትክክለኛው የምርመራ ሂደት በሚገባው ፍጥነት እየተከናወነ አይደለም በሚል ቅሬታን ደጋግሞ ማሰማቱ የሚታወስ ነው፡፡



