ማክሰኞ ነሐሴ 01 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ህዝቦች አቢዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ዋና ጸሃፊ ደስታ ጥላሁን ከፓርቲው መልቃቸውን ገልጸዋል፡፡
የቀድሞዋ ዋና ጸሃፊ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከነባራዊው የፖለቲካ አውድ ጋር እራሳቸውን ማስማማት ያልቻሉና እርዕዮተአለማዊ መከንቸር ውስጥ የገቡ መሆናቸው ፓርቲውን ወደ ፊት እንዲራመድ እንዳላስቻለውም ነው የጠቆሙት፡፡
በተለያዩ ወቅቶች የምሰነዝራቸውን አስተያየቶችና የማቀርባቸውን ሃሳቦች የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ከመቀበል ይልቅ በቸልተኝነት ማለፍን መርጧል ሲሉ የወቀሱት ወ/ሮ ደስታ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ስራቸውን መስራት አዳጋች እንደሆነባቸውም ጠቅሰዋል፡፡
ዋና ጸሃፊዋ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታም ከዚህ በኋላ በፓርቲ ፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ተሳታፊ እንደማይሆኑ ገልጸው በፖለቲካው መድረክ ግን መሳተፍ እንደማያቆሙ አስታውቀዋል፡፡
ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በነበራቸው ውይይት እኚህ ፖለቲከኛ ሞጋች የሚባሉ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በማቅረባቸው በወቅቱ መነጋገሪያ ሆነው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ለአብነትም እርሶ ንጉስ ነዎት? ወይስ ጠቅላይ ሚኒስትር? ሲሉ በወቅቱ ያቀረቡት ጥያቄ የሚታወስ ነው፡፡



