ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለህወሓት የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ሰጠ 

0
362

አርብ ሐምሌ 03 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት “በልዩ ሁኔታ” መስጠቱን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

ይሁን እንጂ ቦርዱ ህወሓት ያቀረበለትን “የቀድሞውን ህልውና ወደነበረበት የመመለስ” ጥያቄ አለመቀበሉን አስታውቋል።

ምርጫ ቦርድ፤ ህወሓት “ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጻ ተግባር ላይ መሳተፉን” እንዳረጋገጠ በመጥቀስ የፓርቲውን ህጋዊ ሰውነት” የሰረዘው በጥር 2013 ዓ.ም ነበር።

የፍትሕ ሚኒስቴር በምርጫ ቦርድ ለተነሳው የህግ ክፍተት ምላሽ የሚሰጥ የአዋጅ ማሻሻያ በማዘጋጀት ባለፈው ግንቦት ወር በፓርላማ ማጽደቁ ይታወቃል።

ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ጥያቄ ከመረመረ በኋላ ባሳለፈው ውሳኔ፤ ህወሓት በድጋሚ ያቀረበለትን ይህን ጥያቄ አለመቀበሉን አስታውቋል።

ቦርዱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅን በማስረጃነት በማቅረብ ነው።

አዋጁ “በአመጽ ተግባር ተሰማርቶ ለተሰረዘ ፓርቲ የቀድሞውን ህልውና መልሶ የሚሰጥ የህግ ድንጋጌ ያልያዘ መሆኑ” በምርጫ ቦርድ መግለጫ ተጠቅሷል።

ሆኖም የአዋጅ ማሻሻያው “በአመጽ እና በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ” የፖለቲካ ፓርቲዎችን “በልዩ ሁኔታ” እንዲመዘገቡ የሚያስችል ድንጋጌን በውስጡ አካትቷል።

“አንድ የፖለቲካ ቡድን ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ውስጥ የተሳተፈ እንደሆነ እና ይህንን ተግባር ማቆሙን እና ሕገ መንግስታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱ በሚመለከተው የመንግስት አካል ከተረጋገጠ፣ የፖለቲካ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል” ሲል አዋጁ ይደነግጋል።

ይህንኑ ማረጋገጫ ከፍትሕ ሚኒስቴር ማግኘቱን ምርጫ ቦርድ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። ማረጋገጫውን ያገኙ የፓለቲካ ቡድኖች፤ ለምርጫ ቦርድ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው በአዋጅ ማሻሻያው የተጠቀሱ ሰነዶችንም ህወሓት ከማመልከቻው ጋር አያይዞ ማስገባቱንም ቦርዱ ገልጿል።

ህወሓት ለቦርዱ ያቀረባቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲው ፕሮግራም፣ የመተዳደሪያ ደንብ፣ የፓርቲው ኃላፊዎች ስምና ፊርማ የያዙ ሰነዶችን ነው።

ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ እነዚህን ሰነዶች መሰረት በማድረግ “ህወሓት በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ” መወሰኑን በዛሬው መግለጫው ይፋ አድርጓል።

ለህወሓት የሚሰጠው የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ “በልዩ ሁኔታ” የሚል ቃላት የተካተተበት እንደሆነም ገልጿል።

ምርጫ ቦርድ በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ያወጣው እና የቦርዱን ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉን ፊርማ የያዘው የምስክር ወረቀትም ይህንኑ በጉልህ ይዟል።

“ይህ የክልላዊ ፓርቲ በልዩ ሁኔታ የምዝገባ እና ህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ፤ ለህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ዛሬ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ተሰጥቶታል” ይላል።

ህወሓት በልዩ ሁኔታ የመመዝገቡን ውሳኔ የያዘ ደብዳቤ ከደረሰው ከዛሬው ዕለት ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራቶች ውስጥ፤ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግም ምርጫ ቦርድ ቀነ ገደብ አስቀምጧል። “የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች በተገኙበት” መደረግ እንዳለበት በተገለጸው በዚሁ ጉባኤ ላይ፤ ፓርቲው “መተዳደሪያ ደንቡን እንዲያጸድቅ” እና “አመራሮችን እንዲያስመርጥ” ምርጫ ቦርድ ውሳኔ አስተላልፏል።

ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን የቅድመ ጉባኤ ዝግጅት የተመለከቱ ስራዎችን ለመከታተል እንዲረዳው፤ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤው የሚያደርግበትን ዕለት ከ21 ቀናት በፊት አስቀድሞ ማሳወቅ እንዳለበትም ቦርዱ በዛሬው መግለጫው አሳስቧል።

ህወሓት የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ከመተላለፉ አስቀድሞ ባወጣው መግለጫ፤ ጠቅላላ ጉባኤውን በሐምሌ ወር መጨረሻ እንደሚያካሄድ አስታውቆ ነበር።

ፓርቲው የጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅቱን መቀጠሉን በየጊዜው በሚያወጣቸው መግለጫዎች ቢያስታውቅም፤ ጉባኤው መቼ እንደሚካሄድ ግን እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።

የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፤ አስቀድሞ በታቀደው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንደማይሳተፉ አዲስ ማለዳ በዛሬው ዜና ጥንቅሯ መዘገባ ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here