ህወሃት በቅርቡ ሊያደርግ እየተዘጋጀ ያለውን 14ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤን በተመለከተ በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በኩል የሚታየው መከፋፈል እንደቀጠለ ነው፡፡ ከጉባኤው እራሳቸውን የሚያገሉ የፓርቲው አባላት መብዛታቸው ተከትሎም የክልሉ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ወዴት እያመራ ነው የሚለው ለብዙዎች ጥያቄ ሆኗል ፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ፓርቲያቸው በቅርቡ ሊያደርግ ካቀደው ድርጅታዊ ጉባኤ ራሳቸውን ማግለላቸውን ይፋ ማድረጋቸውም ይታወሳል፡፡
አቶ ጌታቸው፤ ፓርቲው ድርጅታዊ ጉባኤ ለማድረግ እያካሄደ ያለውን ዝግጅት “በአንድ አካል እየተፈፀመ ያለ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ” ሲሉ ነበር ያወገዙት፡፡
የፓርቲው የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን አባላትም ጉባኤው “ድርጅቱ ውስጥ ‘በተሰባሰቡ ከፍተኛ አመራሮች ተጠልፏል” በማለት ራሳቸውን ማግለላቸውን ከሁለት ሳምንት በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ማድረጋቸውን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።
የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳም በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት ከድምጺ ወያነ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ጉባኤው በአሁኑ ወቅት መካሄዱን እንደማይደግፉ አመልክተው ነበር።
በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በዚህ ጉባኤ የሚታደሙ ተሳታፊዎች መረጣ እየተካሄደ ቢሆንም እራሳቸውን የሚያገሉት አባላት መበራከታቸው እየተስተዋለ ነው፡፡
ሰባት የመቐለ ከተማና ሁለት የትግራይ ማእከላዊ ዞን ከፍተኛ ካድሬዎች ” ጠባብ ቡድን ” ሲሉ በጠሩት አካል ተጠርቷል ባሉት የህወሓት ጉባኤ እንደማይሳተፉ ማስታወቃቸው አለመግባባት ላይ እንዳሉ የሚያመላክት ነው፡፡
በተመሳሳይ “ህወሓትን ለማፍረስ አልሞ በሚካሄደው ጉባኤ አንሳተፍም ” ያሉት 14 የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ” ጉባኤውን ተከትሎ ለሚመጣው ነገር እኛ የለንበትም” በማለት እራሳቸውን ማግለላቸውንም አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ በሚደረገው ጉባኤ ላይ ላለመሳተፍ በተመሳሳይ ሁኔታ እንደምክንያት የተቀመጠው ጉባኤው የሚካሄድበት ጊዜ ትክክል ያልሆነ እና “የጠባብ ቡድን” በሚል የተጠራውን አባላት ጥቅም ብቻ ያማከለ ነው የሚል ነው፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ እና የምዝገባ ጥያቄ የክልሉ ሌላኛው ውዝግብ ነው፡፡
ህወሓት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መነሳቱን ተከትሎ የተሰረዘበት እውቅናው እንዲመለስለት ለምርጫ ቦርድ ያቀረበውን ጥያቄንም በተመለከተ አለመግባባቶች መኖሩ ተመላክቷል፡፡
ፓርቲው ይህንን ጥያቄውን ያቀረበው ከሁለት ሳምንት በፊት ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ነበር፤ፓርቲው በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ የለጠፈው ድብዳቤ፤ “ቦርዱ የድርጅቱን ሕጋዊ ሰውነት ወደነበረበት እንዲመልስ” መጠየቁን የሚያሳይ ነው፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 03 ቀን 2016ዓ.ም ለህወሓት በልዩ ሁኔታ የምዝገባና የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሰጥቷል፡፡
በአዋጅ ማሻሻያው “በአመጽ እና በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ” የፖለቲካ ፓርቲዎችን “በልዩ ሁኔታ” እንዲመዘገቡ የሚያስችል ድንጋጌን በውስጡ አካትቷል።
“አንድ የፖለቲካ ቡድን ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ውስጥ የተሳተፈ እንደሆነ እና ይህንን ተግባር ማቆሙን እና ሕገ መንግስታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱ በሚመለከተው የመንግስት አካል ከተረጋገጠ፣ የፖለቲካ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል” ሲል አዋጁ ይደነግጋል።
ምርጫ ቦርድ ጉዳዩን በማስመልከት በሰጠው መግለጫ ህወሓት የፓርቲው ኃላፊዎች ስምና ፊርማ የያዘ ሰነድ ማቅረቡን ይፋ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፤ እኛ ደግሞ ለዚሁ ምዝገባ ብለን የፈረምነው ምንም ዓይነት ሰነድ ሳይኖር ግለሰቦች በቡድን ተደራጅተው ከድርጅቱ አሰራር ውጭ የፈፀሙት ያልተገባ ተግባር መሆኑን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ኮንነዋል፡፡
ይህን ተከትሎ የትግራይ ክልል ጊዜዓዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው እረዳ የምዝገባ ጥያቄውን የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ የማያውቀው ነው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ አማኑኤል አሰፋ ህወሓት የተሰረዘው ሕጋዊ እውቅናው እንዲመለስለት እንጂ እንደ አዲስ መመዝገብ እንደማይፈልግ ተናግረው ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንዲሁም የህወሃትን ጥያቄ በተመለከተ ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
አገልግሎቱ በዛሬው መግለጫው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቋም ህወሃት እንደማንኛውም አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ በሚመሰረትበት ስርዓት እና አግባብ መሰረት እንደ አዲስ ፓርቲ በመደራጀት ሊመዘገብ እና እውቅና ሊያገኝ ይችላል የሚል እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
በአንጻሩ የፓርቲው አቋም ደግሞ ነባር እና እድሜ ጠገብ የፖለቲካ ድርጅት ስለሆነ እንደ አዲስ ፓርቲ ልመዘገብ አይገባም ጉዳዩ የሕግ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ስለሆነ የተለየ የፖለቲካ ውሳኔ ይፈልጋል የሚል መሆኑን ጠቅሷል፡፡
ምርጫ ቦርድ፤ ህወሓት “ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጻ ተግባር ላይ መሳተፉን” እንዳረጋገጠ በመጥቀስ የፓርቲውን ህጋዊ ሰውነት” የሰረዘው በጥር 2013 ዓ.ም ነበር።
በክልሉ በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የሀሳብ ልዩነት እንዲሁም ፖለቲካዊ መሳሳቦች የክልሉን የወደፊት እጣፈንታ ጥያቄ ውስጥ እንደሚከተውም በብዙዎች ይነገራል፡፡



