
ሰኞ ነሐሴ 06 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከህወሓት ጉባኤ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለድርጅቱ ዛሬ ደብዳቤ መጻፉን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።
ፓርቲው የቦርዱ ደብዳቤ እና የምስክር ወረቀት ከደረሰው ቀን ጀምሮ የሚተዳደረው የኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፖርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011ና ይህን አዋጅ ባሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1332/2016 እንዲሁም እነዚህን አዋጆች መሰረት ተደርገው በወጡ መመሪያዎችና የቦርዱ ውሳኔዎች መሰረት እንደሆነ አስገንዝቧል።
ቦርዱ ውሳኔ የሰጠባቸውና በደብዳቤ ከገለፃቸው በፓርቲው መተግበር ካለባቸው ተግባራት መካከል ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ከማድረጉ ከ21 ቀን በፊት ለቦርዱ ማሳወቅና ፖርቲው በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባኤ የቦርዱ ታዛቢዎች መገኘት በዋናነት የተገለፁ ግዴታዎች እንደሆኑ አመልክቷል።
ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት ፖርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ሊያደርግ መሆኑን ቦርዱ በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን እየተዘገበ እንደሆነ ተረድቻለሁ ብሏል።
በዚህም ቦርዱ ” ለአንድ ጠቅላላ ጉባኤ መደረግ አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እንዲያውቅ ባልተደረገበት፣ ባልተከታተለበትና ባላረጋገጠበት እንዲሁም የቦርዱ ታዛቢዎች ባልተገኙበት ተጠራ የተባለው ጠቅላላ ጉባኤ ሊካሄድ አይችልም ” ሲል አሳውቋል።
ጠቅላላ ጉባኤው ከቦርዱ ፍቃድ ውጭ ከተካሄደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለዚህ ጉባኤም ሆነ በጉባኤዎቹ ላይ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች በሙሉ ዕውቅና የማልሰጥ መሆኑን እወቁት ሲል ለህወሓት በጻፈው ደብዳቤ አሳስቧል።


