“በህወሓት እና ጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል ያሉ ቁርሾዎች በክልሉ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል” ሲል ኢዜማ አስተወቀ

0
576

ማክሰኞ ነሐሴ 07 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በህወሓት እና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል “አሉ” ያላቸው ቁርሾዎች በክልሉ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ስጋት መደቀናቸውን አስታውቋል።

ፓርቲው ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ የፌደራል መንግስት እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የዜጎችን ሰላም እና ደህንነትን ከምንም ጉዳይ በፊት ትኩረት እንዲሰጡ አሳስቧል።

ኢዜማ በዚህ መግለጫው “በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የውስጥ አሰራር እና ሒደት ላይ አሰተያየት መስጠት” ፍላጎቱ አለመሆኑን ጠቅሶ፣ ነገር ግን “እብሪተኛ” ሲል በሚነቅፈው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ምክንያት በትግራይ ክልል እና አጎራባች ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ንፁሐን ዜጎች ላይ ይዞ ሊመጣ የሚችለው አደጋ ቀላል አለመሆኑን ገልጿል።

ፓርቲው አክሎም፣ ህወሓት እንደፓርቲ ሕልውናውን ለማስቀጠል እያደረገው ባለው ሂደት ሳቢያ፣ እንዲሁም የፓርቲው አመራሮች የእርስ በእርስ ሽኩቻ፤ በህወሓት እና ጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል አሉ ባላቸው ቁርሾዎች የተነሳ በክልሉ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል ሲል አሳስቧል።

“የፕሪቶሪያው ሰምምነት በአግባቡ አለመከበሩ በክልሉ ለሚስተዋለው ስር የሰደደ ስጋት፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት መጥፋት ዋነኛ መንስኤ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም” ያለው ኢዜማ፣ “የፕሪቶሪያው ስምምነት በተያዘው ዝርዝር ዕቅድ መሰረት አለመፈጸሙን ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ የመሣሪያ አይነት እና ቁጥር በፖለቲካ ኃይሎች እጅ ባለበት ሁኔታ፣ የሃሳብ ልዩነትን ሰላማዊ በሆነ መንገድ በውይይት መፍታት በማይታወቅበት፣ ብሎም መንግስት እና ፓርቲ የመለየት ምንም የረባ ልምድ በሌለው ፖለቲካችን ውስጥ ሕዝብ የሚያስተዳድር ፓርቲ በውስጡ ያሉ መካረሮች ዳፋው ለሰፊው ሕዝብ እንደሚተርፍ ትናንታችንን ዞር ብሎ ማየት በቂ ነው፡፡” ብሏል።

ኢዜማ የትኛውንም ዓይነት ልዩነት በውይይት እና ሕጋዊ መንገድ ከመፍታት ውጪ ያለው አማራጭ ሁሉ ውጤቱ የዜሮ ድምር መሆኑን በመጠቆም፣ አሁንም ቢሆን በጥይትና ጠመንጃ ማሰብ ጊዜው ያለፈበት ያረጀ ያፈጀ መንገድ መሆኑን አውስቷል፡፡

እንዲሁም “እኔ ያልኩት ብቻ ‘ካልሆነ’ የሚል ግትር መንገድን መከተል ጦረኝነት፣ ግጭት መጥመቅ እና እልቂት መጋበዝ መሆኑን በመረዳት በሰከነ መንገድ ማሰቡ ይሻላል እንላለን” ሲል ጥሪ ስለ ማስተላለፉ አዲስ ማለዳ ዛሬ አመሻሽ ላይ ፓርቲው ካወጣው መግለጫ ተመልክታለች።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here