ማክሰኞ ነሐሴ 14 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የቀድሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አመራሮች ‹‹የንጋት ኮኮብ›› የተባለ አዲስ ፓርቲ ማቋቋማቸው ተነግሯል፡፡
የቀድሞ የፓርቲው ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋና ሃብታሙ ኪታባን ጨምሮ ሌሎች ፖለቲከኞች አዲስ ፓርቲ ሟቋቋማቸውን አዲስ ማለዳ ከፊት አውራሪ የፓርቲው አደራጆች እና የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ምንጮቿ አረጋግጣለች፡፡
ከቀድሞ የኢዜማ አመራሮች በተጨማሪ አዳዲስ ወጣት ፖለቲከኞች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ መምህራን በፓርቲው መካተታቸውን የገለጹልን ምንጮች ፓርቲው ከምርጫ ቦርድ የቅድመ ምዝገባ ፍቃድ ማግኘቱንም ነው የገለጹት፡፡
አቶ የሺዋስ አሰፋና ሌሎችም ፖለቲከኞች ከኢዜማ እራሳቸውን ካገለሉ በኋላ ከፖለቲካው መድረክ እራሳቸውን አጥፍተው ስለሚመሰርቱት አዲስ ተፎካካሪ ፓርቲ ዙሪያ ሲመክሩ መቆየታቸውን አቶ የሺዋስን ጨምሮ ሌሎች በአዲሱ ፓርቲ የተካተቱ የቀድሞ የኢዜማ አመራሮች መናገራቸው ይታወሳል፡፡
‹
አዲስ የተመሰረተው የንጋት ኮኮብ ፓርቲም ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በውጭ የሚገኙ ጉምቱ ፖለቲከኞችንም ስለማካተቱ ለአዲስ ማለዳ የደረሳት መረጃ ያመላክታል፡፡
የቀድሞ ኢዜማ ምክትል መሪ አንዷለም አራጌ በአዲሱ ፓርቲ ውስጥ በመስራችነትም ሆነ አባልነት ያልተካተቱ ሲሆን በ2014 የኢዜማ መሪ ለመሆን ከሃብታሙ ኪታባ ጋር ተጣምረው የፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን አመራር ለመተካት እልህ አስጨራሽ ውድድር አድርገው ከተሸነፉ በኋላ ፊታቸውን ወደ ትምህርት በማዞር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል የድህረ ምረቃ ትምሀርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ሰምታለች።



