የዘመናዊ የአጥንት እና መገጣጠሚያ ህክምና ቢስፋፋም በባህላዊ የአጥንት ህክምና ምክንያት የሚመጣው የጤና ችግር ከምንጊዜውም በላይ በመወሳሰብ ላይ ይገኛል ተባለ

0
397

ማክሰኞ ነሐሴ 21 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ የዘመናዊ የአጥንት እና መገጣጠሚያ ህክምና ቢስፋፋም በባህላዊ የአጥንት ህክምና ምክንያት የሚመጣው የጤና ችግር ከምንጊዜውም በላይ በመወሳሰብ ላይ ይገኛል ሲል ኢትዮጵያን ሶሳይቲ ኦፍ ኦርቶፔዲክስ ኤንድ ትራውማቶሎጂ ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት 10 አመታት የአጥንት ህክምና እንደመስፋፋቱ ከባህላዊ አጥንት ህክምና ጋር ተያይዘው የሚመጡ ውስብስብ የጤና ችግሮች መቀነስ ሲገባቸው በተቃራኒው እየጨመሩ የሚገኙ በመሆናቸው ይህን ተቃርኗዊ የማይጠበቅ ግንኙነት ለማወቅ ይረዳ ዘንድ ቦሳድ የተባለ ሀገር አቀፍ የጥናት እና ምርምር ቡድን መመስሩ ተመላክቷል፡፡

በዋናነትም ቦሳድ(Bone Setting Associated Disability) የጥናት ቡድን ትኩረቱን ያደረገው በሚከሰቱ የአጥንት እና መገጣጠሚያ ጉዳቶች በባህላዊ መንገድ ለማከም የሚደረግ ጥረት ይዞት የሚመጣውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል መፍትሄ ላይ መሆኑ ተገልጻል፡፡

በሌላ በኩል በጤና ተቋማት ውስጥ በየእለቱ በርካታ ታካሚዎች ቀላል የሚባል የአጥንት እና መገጣጠሚያ ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ ወደ ባህላዊ የአጥንት ህክምና በመሄድ ለተለያዩ ውስብስብ የጤና ችግሮች ተጋልጠው ሲመጡ ማየት የተለመደ ነዉ ያለው የህክምና ማህበሩ እነዚህ ውስብስብ የጤና ችግሮች መታከም ከሚችሉ እስከ ቋሚ የአካል ጉዳት አልፎም ተርፎም እስከ ሞት ሲያደርሱ ይስተዋላል ብሏል።

እነዚህ የጎንዮሽ የጤና እክሎች ታካሚው ምንም አይነት ህክምና ሳያገኝ ቤቱ ቢቆይ እንኳን ላይከሰቱ የሚችሉ ናቸው ያለው የጤና ማህበሩ የችግሩን ስፋት እና ጥልቀት ለማወቅ ያስችል ዘንድ በሃገር አቀፍ ደረጃ ጥናት እንድናደርግ ካደረጉን ምክንያቶች ዉስጥ አንዱ ነው ብሏል።

ይህን የጥናት ቡድን ለመመስረት እንደምክንያት ከተቀመጡት መካከል በባህላዊ የአጥንት ህክምና ምክንያት የሚመጣ ውስብስብ ችግር ከዘመናዊ ህክምና ጋር ያለውን ተቃርኖ ማሳወቅ እና ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ይጠቀሳሉ።

የኢኮኖሚ አቅምን ያገናዘበ እንዲሁም ደህንነቱ የተረጋገጠ ዘመናዊ የአጥንት እና መገጣጠሚያ ህክምናን መስጠት የቡድኑ ዋና ዓላማ መሆኑ ተመላክቷል።

ቦሳድ የጥናት ቡድንም ቀጣይ ለሚኖሩ የትግበራ እንቅስቃሴዎች የሚጠቅሙ የተለያዩ ማስረጃዎችን እና መረጃዎችን አዘጋጅቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here