
ረቡዕ ነሐሴ 2ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ፥ በሶማሊያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢ ነው ብሏል።
ሚኒስቴሩ መግለጫውን ያወጣው ግብጽ ከሶሰት አስርት አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሶማሊያ የጦር መሳሪያ መላኳ ከተነገረ በኋላ ነው።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት ከሶማሊያ ጋር ግንኙነቷ ሲሻክር፥ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ ውስጥ ያለችው ግብጽ ለሶማሊያ ድጋፏን አሳይታለች።
ግብጽ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከሞቃዲሾ ጋር የደህንነት ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን በሶማሊያ ለሚሰማራው አዲስ የሰላም አስከባሪ ተልእኮ ወታደሮች ለመላክ ፈቃደኝነቷን መግለጿም ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ አመታት ወታደሮቿን በሶማልያ በመሰማራት ሶማሊያ ጠንካራ ሃገረ መንግስት እንዲኖራት የማድረግ እና ሲቪል ዜጎችንም ከአልሻባብ ሀይሎች ጥቃት የመከላከል ስራ በመስራት ውድ ልጆቿን መገበሯ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ ” የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መልካም ስምና ዝናን እንዲሁም መስዋዕትነት የሚያጠለሹ ተከታታይ መግለጫዎች ሲወጡ ኢትዮጵያ በዝምታ እንድታልፍ ከአንዳንድ ወገኖች በኩል ፍላጎት መኖሩ ይታያል ” ብላለች።
ሌሎች ተዋናዮች የአፍሪካ ቀንድ ክልልን ለማተራመስ እርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ በዝምታ እንደማትመለከት አሳውቃለች።
ይህም በመሆኑ በቀጣናው የብሄራዊ ደህንነቷን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ሁሉ በንቃት እየተከታተለች እንደሆነም አመልክታለች።
የሶማሊያ መንግስት በቀጠናው ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች ከማጠናከር ይልቅ ቀጠናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ኢትዮጵያ አጽንኦት ሰጥታ ገልጻለች።
በሶማሊያ ለማሰማራት የታቀደውን አዲስ የሰላም ተልዕኮ የማዘጋጀትና የመፍቀድ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ሁሉ በቀጠናው የሚገኙና ቀደም ሲል ወታደር አዋጭ የሆኑ አገራትን ተገቢ የሆኑ ስጋቶች ሁሉ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ብላለች።
ኢትዮጵያ ፥ ” ለአጭር ጊዜ ፍላጎታቸውና ከንቱ አላማቸው ሲሉ በክልሉ ውጥረትን ለማቀጣጠል የሚሞክሩ ኃይሎች ዕኩይ ተግባራቸው የሚያስከትሏቸዉን መዘዞች መሸከም ይኖርባቸዋል ” ብላለች።
ቀደም ሲል አህጉራዊና አለምአቀፋዊ አሸባሪ ቡድኖች ላይ የተገኘውን አበረታች ውጤት አደጋ ላይ የሚጥሉና የሚቀለብሱ ድርጊቶችን እንደማትታገስ ተናግራለች።
ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና ከሶማሊያ ህዝብና ከአለምአቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመከላከል አሁንም ቁርጠኛ አቋም እንዳላት አመልክታለች።



