አርብ ነሐሴ 24 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) አምባሳደር ተሾመ ሹንዴ ለሶማሊ ላንድ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የሹመት ደብዳቤያቸውን ማቅረባቸው ተነግሯል።
አምባሳደሩ ለሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ከኢትዮጵያ መንግስት የተላከ የሹመት ደብዳቤና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) የተላከ መልእክትም አድርሰዋል።
አምባሳደር ተሾመ ሃርጌሳ ደርሰው የሹመት ደብዳቤያቸውን ሲያቀርቡ በፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የሶማሌላንድ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ለአዲሱ አምባሳደር የእንኳን ደህና መጡ መልካም ምኞታቸውን ገልፀው በቆይታ ግዜያቸው ለሁለቱ ሀገራት አንድነት ፣ ሰላም እና የጋራ ጉዳዮች ለሚሰሩት ስራዎች የቅርብ ድጋፍ እንደማይለያቸው አረጋግጠዋል።
አምባሳደር ተሾመ ከፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ ጋር በነበራቸው ውይይት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የጸጥታ ጉዳዮች፣ የሁለቱን ወንድማማች ሀገራት ግንኙነት በማጠናከርና የወደፊት ትብብር ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገልጿል።
ይህን ሹመት ተከትሎ እስካሁን ድረስ ከሞቃዲሾ መንግስት በኩል የተባለ ነገር የለም፡፡
በተያያዘም የሱማሌላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የግብጽ ጦር በሶማሊያ መስፈሩን እቃወማለው ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡
የጦሩ በቀንዱ መስፈርም ቀጠናዊ ቀውስን የሚያዋልድ፣ጦርነት የሚቀሰቅስና መሰል መዘዞችን የሚያስከትል ነው ያለው የሚኒስቴሩ መግለጫ ሃርጌሳ ሂደቱን እጇን አጣጥፋ ተቀምጣ አትመለከተውም ብሏል፡፡



