እሁድ ነሐሴ 26 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል አለመወሰን ለሰራተኞች የመኖር እና የአለመኖር ጉዳይ ሆኗል ሲሉ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ አስታወቁ።
በአሁኑ ወቅት በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ሰራተኞች ደመወዝ 5 ሊትር ዘይት እንኳን አይገዛም ያሉት የኢሰማኮ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፤ በተለይ የፋብሪካ ሰራተኞች ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን አብራርተዋል።
አቶ ካሳሁን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲስተካከል የቀረቡ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘታቸውንና በቅርቡም ጥያቄው በድጋሚ ለመንግስት መቅረቡን ተናግረዋል።
ኮንፌደሬሽኑ ከዝቅተኛ ደመወዝ ወለል ባሻገር የገቢ ግብር ቅነሳን የሚመለከት ጥያቄ ቢኖረውም በአፋጣኝ ይመለሳሉ ወይ በሚለው ዙሪያ ስጋት አለው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ለሰራተኛው በቶሎ መልስ ይሰጠው ዘንድ ጠይቀዋል።



