ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ የ2016 ዓመታዊ ኮንፈረንስ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ አድርጓል፡፡
የፓርቲው መሪ የሆኑት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በዚህ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር “የገዢው ፓርቲ አባላት ሆነው የብሔር ፖለቲካ እሳቤ ላይ የተጠመቁ አባላት መኖራቸውን ጠቅሰው ይህ አስተሳሰብ ለአገር እድገት ዋነኛው ጠንቅ እየሆነ ነው ብለዋል፡፡
ብሔር ላይ የተጣበቀ የፖለቲካ ፓርቲ ለህልውና አደጋ ነው ያሉት ብርሀኑ በትግራይ ክልል የሚታየው ውጥንቅጥ መነሻ እና ምንጩም የብሔር ፖለቲካ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
አክለውም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል የሚፈጸም አስፈሪ የሆነው ስርዓት አልበኝነት፣ አፈና እና ግድያ መነሻ እና መድረሻ ምክንያት ያልተገራ የብሔር ፖለቲካ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ እንቅፋት ሊሆኑ እንደሚችሉ ከዚህቀደም ያስቀመጧቸው አካላት በእርግጥም እንቅፋት እንደሆኑ አስታውሰዋል፡፡
ከሶስት ሀይሎች እንቅፋት ሊገጥም ይችላል ያሉ ሲሆን እነሱም ህውሃት እና ተከታዮቹ፣ የለውጡ ባለቤት እኔ ነኝ የሚለው የተረኛ ብሔርተኛ ጽንፍ እና ጽንፈኛ የአንድነት ሀይል ናቸው ሲሉ የፓርቲው መሪ ገልጸዋል፡፡



